Monday, August 17, 2009

 

ቴዲ አፍሮ ተፈታ - አንድ ብለናል። ብርቱካን ትቀጥል !

ግርማ ካሳ (muziky68@yahoo.com)
ነሐሴ 18 2001

ሰሞኑን የተፈጠረዉን ክስተት ከግምት ዉስጥ በማስገባት ኅዳር 24 ቀን 2001 ዓ.ም፣ «የቴዲ አፍሮ መታሰር በኢትዮጵያዊነት ላይ ያነጣጠረ ነዉን ?» በሚል አርዕስት ያቀረብኩትን ጽሁፍ አሻሽዬ እንደሚከተለዉ ለኢትዮጵያዊያን አንባቢያን አቅርቢያለሁ።

ከአሥራ አራት ዓመታት ስደት በኋላ አገሬን ለማየት ግንቦት ሰባት 1997 ዓ.ም. አዲስ አበባ ገባሁኝ። የታሪካዊውን ምርጫ ሁኔታ ለመከታተል ዕድል አግኝቼ ነበር። ያኔ ስለተደረገዉ ምርጫ አሁን ብዙም ማወራት አልፈልግም። ነገር ግን ከፒያሳ ወደ መገናኛ ለመሄድ ሚኒባስ ውስጥ ገብቼ ያጋጠመኝን አንድ የማልረሳዉ ክስተትት ላጫውታችሁ እፈልጋለሁኝ።

አውታንቲው “መገናኛ፣ ኮተቤ፣ …” እያለ ተሳፋሪዎችን ይጠራል። ትንሽ እንደቆየን ሚኒባሱ ይሞላና ጉዞ እንጀምራለን። ከጎኔ አንዲት ወጣት ሴት ነበረች። ትንሽ እንደሄድን እንባ በዓይኔ መፍሰስ ጀመረ። ከዚህ በፊት ሰምቼ የማላውቀው አይነት በሬጌ ቢት የቀረበና ልብን የሚሰበር ቃላት ያሉት ዜማ ሹፌሩ ያጫውት ጀመር። “ይሄ ማን ነው?” ብዬ ከጎኔ ያለችውን ወጣት ጠየቅኋት። በመገረም አይታኝ “ቴዲ አፍሮ ነዋ!” ብላ መለሰች። ብዙ ጊዜ መንፈሳዊ መዝሙሮችን ስለምሰማ ድሮ ከማውቃቸው ከእንደነ ነፃነት መለሰ - ‘አረንቻታ’ እና ከቴዎድሮስ - ‘ጉዱሮዬ’ ውጭ ብዙም የዘመኑ የኪነት ባለሞያዎችን አላውቃቸውም ነበር።

ይቅር በለውና የበደለን ወቅሰህ፣
ምህረት አስተምረን አንድ አርገን መልሰህ
ዘጸዓት ለኢትዮጵያ ወደ ተስፋ ጉዞ፣
ባህር የሚያሻግር አንድ ሙሴ ይዞ
ቅርብ ነው አይርቅም የኢትዮጵያ ትንሳዔ፣
በአንድነት ከገባን የፍቅር ሱባዔ
ፍቅር አጥተን እንጅ በረሃብ የተቀጣን፣
አፈሩ ገራገር ምድሩ መች አሳጣን
ኦሲሳ ኦሲሳ ኦሲሳ ማንዴላ፣
ይቅር አባብሎ እንዳስጣለ ቢላ
በተስፋዋ መሬት እንዲፈጸም ቃሉ፣
ሞፈሩን ያዙና ይቅር ተባባሉ …”

እያለ ነበር ቴዲ አፍሮ የሚያቀነቅነው።
ትዝ ይለኛል በምርጫው ውዝግብ ወቅት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ይህን በኔ ግምት እንደ ኢትዮጵያ የሕዝብ መዝሙር ሊቆጠር የሚገባውን ዜማ እያዜሙ ነበር የምርጫ ዘጠና ሰባት መሰረቅ ላይ ያተኮረውን ተቃውሟቸውን የገለጹት።

የዜማው መልዕክት ግልጽና ቀጥተኛ ነው። አገራችን ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሃብት ያደላት፣ ከማንም አገር በምንም የማትተናነስ እንደሆነች፣ እኛ ኢትዮጵያውያን የደኸየነውና የቆረቆዝነው ፍቅር በማጣታችንና ይቅር መባባል ባለመቻላችን ብቻ እንደሆነ ነው ቴዲ አፍሮ ደስ በሚያሰኝ ቃና የገለጸልን።

እርስ በርስ መገዳደል፣ እርስ በርስ መባላት አይበቃንም ወይ? ነው ያለን። እጅ ለእጃችን ከተያያዝን፣ አንድ ከሆንን፣ በዘር በኃይማኖይት ካተከፋፈልን፣ ከግል ጥቅማችን አልፈን ለወገናችን ካሰብን የኢትዮጵያ ትንሳዔ ቅርብ እንደሚሆንና እግዚአብሔር አምላክም እንደሚታረቀን ነው ያስተማረን። በዚህ ዜማ ኢትዮጵያዊነትን አይቻለሁ። ፍቅርንና መተባበርን አሽትቻለሁ።

ይህ ብቻ አይደለም። ወደ አሜሪካ ከተመለስኩኝ በኋላ አንድ ወዳጄ ቤት እራት ተጋበዝኩኝ። በርካታ ሰዎች ነበሩ። ለካ ሌላ ተመሳሳይ ዘፈን ቴዲ አፍሮ ከዚህ በፊት አውጥቶ ኖሯል፤ ቀልቤን የሳበ በቪዲዮ የተቀነባበረ ዜማ ለማዳመጥ ቻልኩ። በአቴንስ ግሪክ ኦሎምፒክ ወቅት ወገኖቻችን ያሳዩት አኩሪ ዉጤት ላይ ያተኮረና በምሳሌያዊነት የመያያዝንና የመደጋገፍን ጥቅም ለማሳየት የሞከረበት የዜማ ቅንብር ነበር።አንጋፋው ኃይሌ ገብረሥላሴ እግሩን በመታመሙ ወደ ኋላ ሲቀር፤ ቀነኒሳ እና ስለሺ ወደ ኋላ እርሱን ሲመለከቱ ነው ቪዲዮው የሚያሳየው። ወንድማቸው ወደ ኋላ በመቅረቱ ውስጣቸው አዝኖ እግራቸው ወደፊት እየሮጠ ዓይናቸው ወደ ኋላ ይመለከት ነበር።

ኃይሌ ገብረሥስላሴ፡-

“… መርቆ ሸኝቶን አገር፣ አሲዞን ሰንድቅ ዓላማ
መርዶ ነው ለወገናችን ፣ ማሸነፍ ካቃተንም
ብሰለፍ ሕመሜን ችዬ ፣ እሮጬ ላሯሩጣችሁ
ትልቁን እምነት በናንተ ፣ ጥለናል እንግዲህ አይዟቹህ …”
ሲላቸው ስለሺ እና ቀነኒሳ ደግሞ በተራቸው፦

“… እዮሃ ከባንዲራው ነው ፣ እዮሃ ቃልኪዳናችን
እዮሃ አታፍርም በኛ ፣ እዮሃ ኃይሌ አባታችን …”

እያሉ ኢትዮጵያን፤ እንዲሁም “አባታቸውን” ኃይሌን ሲያኮሩ እናያለን። አንዱ ሲደክም ሌላው እያገዘ፣ አንዱ ሲወድቅ ሌላው እየተነሳ፣ በሕብረት፣ በወንድማማችነት፣ እርስ በርስ በመተያየትና በመያያዝ አገራችንን ከውርደት ማንሳት እንደሚቻል ነው የምንማረው። የኢትዮጵያን አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ባንዲራ ከሌሎች አገራት ባንዲራዎች ከፍ ብላ እንድትውለበለብ ማድረግ እንደሚቻል ነው ቴዲ አፍሮ ለማሳየት የሞከረው። ምሳሌው ሩጫ ሆነ እንጂ በሁሉም መስክ ፍቅርና አንድነት ካለን ቀዳሚ የማንሆንበት ምክንያት የለም።

ከላይ የተጠቀሱት ዜማዎች ብቻ አልነበሩም።
«ስማ ስጠራህ በዚህ ማሲንቆ፣ ይጥራ ዘመኑ ሁሉም ሰዉ ታርቆ»
እንኳን አደርሰን ለአዲስ ዘመን፣ ዘመን ጀንበር ነዉ ይዉጣልን
ለዓለም ለአለም፣ እንዳይለያይለን ዘለዓለም”

ሲል ነበር ቴዎድሮስ አፍሮ በአበባየዎሽ ዜማ፣ ኢትዮጵያዉያን ከ1999 ወደ 2000 ዓ.ም በምንሸጋገርበት ጊዜ በፍቅር፣ በእርቅ በአንድነት እንድንሻገር መልካም ምኞቱን የገለጸዉ።

«ሆ በል ማሲንቆ ሆ በል ክራር ዝፈን ላገር፣
ሆ በል ዋሽንት ሆ በል ማሲኦንቆ ስታይ ሰዉ ታርቆ»

ብሎ እያቀነነቀ ነበር ፣ በአገር ዉስጥ ፣ ከአገር ዉጭ፣ በአራት ኪሎ የሚኒሊክ ቤት መንግስት ፣ በእሥር ቤት፣ በከተማ፣ በገጠርን በሚታወቅ አድራሻ ለሚኖሩ፣ የበበረሃዉና በየጫካዉ ነፍጥ አንስተዉ ለሚንቀሳቀሱ ሁሉ ተዲ አፍሮ መልእክቱን ያስተላለፈዉ።

ሰዉ ገጭተሃል በሚል ክስ፣ ቴዲ አፍሮ ወደ እሥር ቤት ከመወረዱ በፊት ደግሞ የሰማነዉ ዜማ፣ ኢትዮጵያዉያን ፊታችንን ወደ እግዚአብሄር እንድንመልስ የሚያስተምርና የሚገስጽ፣ ጌታችንና መድሃኒታችን ኢየሱስ ከርስቶስ በቀራንዩ መስቀል ላይ ስለኛ የከፈለዉን የፍቅር መስዋእትነት የሚያስታወስ መንፈሳዊ ዜማ ነበር።

«አርነት አወጣኝ ቀራንዩ ላይ፣ ስለኔ ብዙ አየ ስቃይ
እዝራ በመሰንቆ ዳዊት በበገና፣ ያከበረህ አምላክ ይድርስህ ምስጋና
ዉዳሴ ለስሙ ላዳነኝ ጌታ፣ በምን ልመልሰዉ የርሱን ዉለታ
ሃሌሃሌሉያ ለታረደዉ ጌታ፣ በምን ልመልሰዉ እኔ የርሱን ዉለታ
ሰማያዊ ጸጋ የማርያም ልጅ፣ በመስቀሉ ዘጋ የሲዖል ደጅ
ባንተ ቦታ ያድርጉኝ ይስቀሉኝ ጌታዬ፣ ስቃይህን ልካፈል ባለዉለታዬ»

እያለ የመላእክት ቋንቋ በሆነው በሙዚቃ አምላኩንና አምላካችንን አከበረ። «ኢትዮጵያያ ታበጽሕ እደዊሃ አብ እግዚባሄር ሃሌሉያ። ሰላም አማን አርጋት አገራችንን » ሲል ምድርና ሰማይን የፈጠረ አምላካ የምህረት እጁን ለአገራችን እንዲዘረጋ፣ በምድራችን የእርቅ የሰላም የመዋደድ መንፈስ እንዲሰፍንም ጸለየ።

ሕግ እናስከብራለን የሚሉ ባለሥልጣናት መረጃ አለን ይላሉ። «ሰዉ ገጭቷል» የሚል ክስ አቅርበዉ ከሁለት አመት በላይ ቴዲ አፍሮ እንዲታሰር ተደረገ። የዚህ ወጣት መታሰር ብዙዎቻችንን አሳዘነ። አስቆጣም።

የስድስት አመት የእሥራት ዉሳኔ ወደ ሁለት እንዲቀየር ተደርጎ በእግዚብሄር ቸረነት ቴዲ አፍሮ የማታ ማታ ተፈታ። እኛም ተደሰትን። ቴዲ አፍሮን፣ የቴዲ አፍሮ ቤተሰቦችና ወዳጅች ሁሉ በዚህ አጋጣሚ «እንኳን ደስ ያላችሁ! እንኳን ደስ ያለን !» እላለሁኝ።

ገዢዉ ፓርቲም ለሕዝባዊ ጥያቄና ጥሪ አዎንታዊ መልስ በመስጠት፣ ብዙዎቻችን ከነበሩን በርካታ ጥያቄዎች መካከል አንዱ የነበረዉ የቴዲ አፍሮ መፈታት ጉዳይ ምላሽ እንዲያገኝ በማድረጉ ምስጋና ላቀርብ እወዳለሁ። የቴዲ አፍሮ መፈታትንም አንድ ብለናል።

ነገር ግን መቀጠል ያለበት ነገር አለ። ሌላዋ የኢትዮጵያ አንድነት፣ የፍትህ፣ የሰላምና የፍቅር ሐዋርያ የሆነችዉ በአሥር ሚሊዮን በሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉያን ዘንድ የምትወደድ፣ ለምታምንበትና ለመርህዎቿ የቆመች፣ ከርሷ ምቾታና ድሎት ይልቅ የአገርን ጥቅም ያስቀደመች፣ አንዲት እህታችን አሁንም ኢፍትሃዊና ኢሰብዓዊ በሆነ መንገድ በቃሊቲ እሥር ቤት ትገኛለች። ይችንም ሴት ገዢዉ ፓርቲ በአስቸኳይ እንዲፈታ፣ ከሌሎች በሚሊዮን የሚቆጥሩ ወገኖቼ ጋር በመሆን አገራዊ ጥሪዬን አቀርባለሁ።

ይህ ሴት ብርቱካን ሚደቅሳ ናት። ኢሕአዴግ በምርጫና ሰላማዊ በሆነ እንቅስቃሴ የሚያምን ከሆነ፣ በሌሎች ዜጎች ላይ ጥይት ተኩሳ ያልገለደችን፣ የአገሪቱን ሕገ መንግስት አክብራ የምትንቀሳቀስን፣ እንዳንዶች «ወያኔ ጠላት ነዉ። መጥፋት አለበት» በሚሉበት ጊዜ «አይደለም። ወያኔም ሆነ ማንም ኢትዮጵያዊ የማንም ሌላ ኢትዮጵያዊ ጠላት አይደለም። በፍቅር በይቅር መባባል አገራችንን በጋራና በሰላም ነዉ መገንባት ያለብን» ብላ ያስተማረችን፣ የአምስት አመት ሕጻን እናትና የሰባ አራት አመት አሮጊት እናት ጧሪን የሆነችዋን፣ ብርቱካን ሚደቅሳን መፍታት ይኖርበታል። ከሁለት አመት በፊት የነበረን ያረጀንና ያከሰመን ክስ በመምዘዝ፣ ገዢዉ ፓርቲ እየተጫወተዉ ያለዉን ጨዋታ አቁሞ ፣ ለአገርና ለሕዝብ የሚጠቅምን፣ በአገራችን ብሄራዊ መግባት እንዲኖር የሚረዳን ሥራ ይስራ እንላለን። ብርቱካን ሚደቅሳ አሁን ትፈታ !!!!

( ስለብርቱካን ሚደቅሳ የበለጠ ለማወቅና ይችንም ሴት ለማስፈታት የሚደረገዉን የተቀደሰ ጥረት ለማገዝ ወደ http://wwww.freebirtukan.org/ ድህረ ገጽ ሄደን መረጃዎች ማግኘት እንችላለን)

Comments:
behind merck acquired were incomplete lean themcreating siren enforce moment prototyper
lolikneri havaqatsu
 
Post a Comment



<< Home

This page is powered by Blogger. Isn't yours?