Friday, July 10, 2009

 

አቶ መለስ ብሄራዊ መግባባት አጀንዳችን ነዉ አሉ!

ግርማ ካሳ (muziky68@yahoo.com)

ሐምሌ 3 ቀን 2001
የአሥራ ሰባት አመት ወጣት ነዉ። ጥይት የጎረሰ ሽጉጥ በእጁ ይዟል። እጅግ በጣም ብዙ ሕዝብ በተሰበሰበበት አደባባይ፣ ንግግር አድርገዉ ወደ ጨረሱ አንድ የእድሜ ባለጸጋ ሰዉ ቀስ በቀስ ይጠጋል። ሳያስቡት የያዘዉን ሽጉጥ ወደ እርሳቸዉ ደቅኖ ይተኩሳል። ሰዉዬዉ ይወድቃሉ። አካባቢዉ ተረበሸ። ተናወጠ። አምቡላንስ ተጠርቶ በአፋጣኝ በስፍራዉ ደረሰ። የወደቁትን አባት በአምቡላንሱ የነበሩ የህክምና ባለሞያዎች አነሷቸዉ። የፍጥነት ጉዞ ወደ ሆስፒታል ጀመሩ። ሆስፒታል ሳይደርሱ በመንገድ ላይ የኝህ ሰዉ ሕይወት አለፈች።

ይህ ወጣት ይጋል አሚር ይባላል። ተኩሶ የገደላቸዉም ሰዉ የቀድሞ የእሥራኤል ጠቅላይ ሚኒስተር ይሳቅ ራቢን ነበሩ።

ይሳቅ ራቢን እድሜ ዘመናቸዉን በሙሉ የጥይትና የመድፍ ድምጽ በመስማት ያሳለፉ ጦረኛ ወታደር ነበሩ። በፈረንጆች አቆጣጠር በ1941 ከታዋቂዉ ሞሼ ዳያን ጋር የፓልማክ ግብረኃይል አባል ሆነዉ፣ ያኔ በፍረሳንዮች ቅኝ ግዛት ስር በነበረችዉ በሊባኖስ የናዚ ጀርመን ደጋፊ የነበረዉ የፈረንሳይ ቪቺ መንግስት ወታደሮች ጋር ተዋግተዋል። በዚያ ጦርነት ጊዜ ነበር ሞሼ ዳያን አንድ አይናቸዉን ያጡት።

ከዚያ በኋላ ከአረቦች ጋር በተደረጉት ተከታታይ ጦርነቶች ትልቅ ጀግንነትና የዉትድርና ብቃት ያሳዩ፣ በእሥራኤል ታሪክ አሉ ይባሉ ከነበሩት ታላቅ የጦር መሪዎች አንዱ ነበሩ። የእሥራኤል የመከላከያ ሚኒስቴር፣ የጦሩ የኢታ ማጆር ሹም ሆነውም አገልግለዋል።

ይሳቅ ራቢን «እኔ ሰላም ሳላይ እድሜዪን ጨርሻለሁ። ለልጆቻችን ሰላም ማምጣት አለብን» በሚል እምነት፣ ድፍረት የተሞላበት የሰላም እርምጃ ወሰዱ። የእሥራኤል ጠላቶች ከሚባሉ ጋር መነጋገር ጀመሩ።

ኢሳቅ ራቢን ከመገደላቸዉ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት የተናገሩት፣ ለእኛ ለኢትዮጵያዉያንና ለመሪዎቻችን ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ አስደናቂ አባባል ነበር ። «የሰላም መንገድ ከጦርነት ይሻላል። ይሄን የምለዉ እንደ አንድ ወታደር ነዉ። መከላከያ ሚኒስቴር ሆኜ የእስራኤል ወታደሮች ቤተሰቦች ስቃይ ይሰማኛል። ለነርሱ፣ ለልጆቻችን፣ ለልጅ ልጆቻችን ስንል መንግስታችን ዘላቂ ሰላም እንዲገኝ ማንኛዉንም ቀዳዳ፣ ማንኛዉንም እድል መጠቀም አለበት። ሰላም አንድ ጸሎት ብቻ አይደለም። ሰላም የጸሎታችን መጀመሪያ ነዉ» ነበር ያሉት።

የጦርነትን ፣ የጥላቻና የእልህ ፖለቲካ አደገኛነቱን ያወቁታልና፣ አብረዋቸዉ የነበሩ ጓደኞቻቸዉ ሲረግፉ፣ አካለ ስንኩል ሲሆን፣ ንብረት ሲወድም ፣ ሰዉ በሰዉ ላይ ሲጨክንና አዉሬ ሲሆን አይተዋልና፣ እርሳቸዉ የኖሩበትን በጦርነት የተበከለን አየር ለልጅ ልጆቻቸዉ ማዉረስ አልፈለጉም። እርሳቸዉ ይመኙትና ይናፍቁት የነበረዉን ሰላም፣ እርሳቸዉ ባያገኙትም እንኳን፣ የልጅ ልጆቻቸዉ እንዲያገኙ መደረግ ያለበትን ሁሉ ማድረግ እንዳለባቸዉ ተገነዘቡ። «ለልጅ ልጆቻችን ስንል ሰላም እንዲመጣ የተገኘችዋን ቀዳዳ ሁሉ መጠቀም አለብን» በሚል ጽኑ አምነት፣ በጦርነት ያልሆነ፣ የወስጥና የልብ ጀግንነት ለማሳየት ተንቀሳቀሱ። የእሥራኤል ጠላት ከተባሉት ከነያሲር አራፋት ጋር መነጋገር ጀመሩ።

ብዙ ተቃዉሞ መጣባቸዉ። እነ ናታንያሁ ተነሱባቸዉ። ግትር ፖለቲካ የሚያራምዱ፣ በጭንቅላት ሳይሆን በጠመንጃ የሚያምኑ፣ እነርሱ ብቻ ከሌላዉ እንደተሻሉ አድርገዉ በመቆጠር በትእቢት የተወጠሩ፣ ከነርሱ ዘር ዉጫ ለሌላዉ ግድ የማይሰጣቸዉ ሰዎች በርሳቸዉ ላይ ማንጎራጎር ጀመሩ።

ኢሳቅ ራቢን ግን ወደ ኋላ አላሉም። «የሰላም ጠላቶች አሉ። ሊጎዱን፣ የሰላሙን መንገድ ሊያጨናግፉን የሚፈልጉ። በድፍረት እናገራለሁ። ከፍልስጤማዉያን መካከል የወጣዉ፣ በፊት ጠላታችን የነበረዉ የፍልስጤም ነጻ አውጭ ግንባር አሁን የሰላም አጋራች ሆኗል» ሲሉ ከቀድሞ ጠላቶቻቸዉ መካከል ወዳጆችን እንዳፈሩ ተናገሩ። ከያሲር አራፋት ጋር በአንድ ላይ ለሰላም ቆሙ። ኢሳቅ ራቢን በጦርነት ሊያጠፉት ያልቻሉትን የያሲር አራፋትን ቡድን በሰላም አሸነፉት።
ታዲያ ለዘመናት በጦር ሜዳ ሲዋጉ በጥይት ያልተመቱት እኝህ ታልቅ ሰዉ፣ በሰላሙ ሜዳ በቴላቪቭ ከተማ ጥይት አገኘቻቸዉ። ለሰላም ለፍቅር ለወንድማማችነት ሲሉ ወደቁ። እጅግ ታሪካዊ፣ ተወዳጅ የሰላም ሰዉ !!!!

የይሳቅ ራቢንን ታሪክ ያለምክንያት አላመጣሁትም። አንዳንዶች ተቃዋሚዎችን መጨፍለቅ ጀግንነት ይመስለናል። አንዳንዶች ኃይልን የምንመዝነዉ በያዝነዉ ብረትና በዘረጋነዉ የሥለላ አዉታር ነዉ። መነጋገር፣ መወያየት፣ ፍቅርና መግባባት ፣ በጦርነትም ሆነ በጉልበት ከሚገኝ ጊዚያዊ መፍትሄ የበለጠ ዘለቆታ ያለዉ ጥቅም ሊያመጣ እንዲሚችል አናስብም። የሩቁን፣ እኛ ካለፍን በኋላ በልጆቻችንና በልጅ ልጆቻችን ዘመን ሊፈጠር የሚችለዉን፣ ለሁላችንም የሚበጀዉን አንመለከትም። ጊዚያዊ ጥቅማችንንና ስልጣናችን ላይ ብቻ በማተኮር ግትር ፖለቲካ እናራምዳለን።

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስተር መለስ ዜናዊ በፓርላም ተገኝተዉ ከተመራጮች ለቀረበላቸዉ ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ አንዲት ቀልቤን የሳበች አባባል አደመጥኩኝ።

ስለ መጪዉ የአገሪቷ ባጀት ነበር በፓርላማ ዉይይት ሲደረግ የነበረዉ። ለጦር ሰራዊቱና ለፖሊስ ከተመደበዉ ባጀት ተቀንሶ ወደ ሌላ ጠቃሚ ፕሮግራም እንዲዉል የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ኅያሎች ሕብረት የፓርላማ ተጠሪ፣ አቶ ገበሩ ገብረማርያም ሃሳብ ያቀርባሉ። ፖሊስና ደህንነት አባላትን በማብዛት ብቻ የአገር ደህንነትን ለማስጠበቅ ከመሞከር ይልቅ የችግሮች ምንጭ የሆኑትን ከሥራቸዉ በንግግርና በሰላም መፍታት ቢቻል የበለጠ ለአገር ጠቀሜታ ይኖረዋል በሚል «ስለ አገር በምናስብበት ጊዜ፣ ስለ እድገት በምናስብበት ጊዜ የብሄራዊ መግባባትን የመፍጠር ጉዳይ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ ቢታይ ከበጀቱም ጋር ከሁሉም በላይ ጠቃሚ ነዉ» ሲሉ ሃሳባቸዉን ያቀርባሉ።

በሕብረቱ ተወካይ ለቀረበዉ ሃሳብ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሲመለሱ «ብሄራዊ መግባባት መፈጠር አለበት የሚባለዉ በራሱ ምክንያት የምንደግፈዉ አጀንዳ ነዉ። የጸጥታ አስከባሪ አቅማችንን በማሽመድመድ የሚፈጠር ብሄራዊ መግባባት ግን የለም። አገሪቱን ለዉጭ ጥቃት አጋልጦ የሚፈጠር የፖለቲካ ትርፍ የለም» አሉ።

እርግጥ ነዉ አገሪቱን ለዉጭ ጥቃት ማጋለጥ ጸረ-ኢትዮጵያዊነት ነዉ። አገሪቷ በአባይ ወንዝ አጠቃቀም ምክንያት ከግብጽ ሊነሳ የሚችልን ጥቃት፣ አልሻባብ የተባለዉ በሶማሊያ የሚንቀሳቀሰዉ ጨካኝ ቡድን ሊያመጣ የሚችለዉን የተወሳሰበ የሽብር አደጋ በአንድነትና በጋራ እንደ ኢትዮጵያዊ መመከት መቻል አለብን። በአዲስ አበባ ስልጣን ላይ ያለዉ መንግስት እኛ የምንወደዉ አለመሆኑ በአገራችን ላይ የመጣዉን አደጋ እንዳናይ አይኖቻችንን ሊሸፍነዉ አይገባም።

ከሰባ አመታት በፊት በቻይና፣ በማኦ ዜዱንግ የሚመራዉ የኮሚኒስት ፓርቲና በኋላ ታይዋንን በመሰረቱት በቺያንግ ካ ሼክ የሚመራዉ የናሽናሊስት ፓርቲ እርስ በርስ ይዋጉ ነበር። ጃፓን ቻይናን በምትወርበት ጊዜ ግን፣ እርስ በርስ ሲዋጉ የነበሩት ወገኖች በአንድነትና በጋራ የዉጭ ወራሪን መመከት ጀመሩ። እኛም ከቻይናዉያን ተምረን የዉስጥ ችግሮቻችንን ከዉጭ ችግሮቻችን መለየት መቻል አለብን እላለሁኝ።

ስለሆነም የአየር ኃይላችንን፣ የምድር ጦራችንን የበለጠ ማጠናከርና ማደራጀት ተገቢና እጅግ አስፈላጊ ነዉ። የአገር አንድነት፣ የአገር ደህንነት ማንም ይግዛ ማንም ቅድሚያ ሊሰጠዉ የሚገባ ጉዳይ ነዉ።

ከባጀት ጭመራዉም ባለፈም መልኩ፣ ሰራዊቱ የኢትዮጵያን ህዝብ ያንጸባረቀ፣ ከፖለቲካ ነጻ የሆነ፣ የግልሰቦችን ጥቅም ሳይሆን የአገርን ጥቅም የሚያስጠብቅ ሰራዊት እንዲሆን በተሻለ መንገድ መዋቀር ይኖርበታል። ኢትዮጵያ ጠንካራ፣ ሁላችንም የምንኮራበትና የምንተማመንበት የመከላከያ ሰራዊት ያስፈልጋታል።

እዚህ ላይ የዉጭ ጥቃት በምልበት ጊዜ ኤርትራን እንደማልጨመር እንዲታወቅልኝ እፈልጋለሁ። ኤርትራዉያን ወንድሞቻችንና ወገኖቻችን ናቸዉ።ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል ናት ብዬ ነዉ የማምነዉ። በሰላም በፍቅር እንደገና አንድ እንሆናለን የሚል ትልቅ እምነት አለኝ። ከኤርትራ ጋር የሚደረግም ጦርነት የወንድማማቾ የርስ በርስ ጦርነት እንጂ ከውጭ ኃይሎች ጋር የሚደረግ ጦርነት አይደለም።

ወደ ፖሊስና የደህንነት አባላት ስንመጣ ግን የተለየ ሃሳብ ነዉ ያለኝ። ለነርሱ በስፋት የሚጨመር ባጀት በምን መልኩ ከዉጭ አገር ከሚመጣ ጥቃት ጋር ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳገናኙት አልገባኝም። አቶ ገብሩ ገብረማርያም እንዳሉት ፖሊስና ሰላዮች ከማብዛት ብሄራዊ መግባባት ላይ ማተኮሩ የበለጠ ይበጃል እላለሁ።

በፓርላማዉ በነበረዉ ክርክር ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ድርጅታቸዉ ብሄራዊ መግባባት ሊኖር እንደሚገባ ሲናገሩ ፡ «ብሄራዊ መግባባት መፈጠር አለበት የሚባለዉ በራሱ ምክንያት የምንደግፈዉ አጀንዳ ነዉ» ነበር ያሉት።

እንግዲህ ከላይ ለማሳየት የሞከርኩት የይሳቅ ራቢን ምሳሌነት እዚህ ላይ ነዉ የሚመጣዉ። እንደ ኢሳቅ ራቢን አሁን በሥልጣን ላይ ያሉት የኢሕአዴግ ባለሥልጣናት ከወጣትነታቸዉ ጀምሮ ጦርነትን ያዩ፣ በጦርነት የኖሩ ሰዎች ናቸዉ። በታሪክ ስለሚኖራቸዉ ቦታ፣ ስለ ልጆቻቸዉና የልጅ ልጆቻቸዉ ማሰባ አለባቸዉ እላለሁኝ።

ጸረ-ሽብርተኝነትን ለመቋቋም ተብሎ የወጣዉ አዋጅ ፣ አባቶቻችን በአድዋ በካራማራ፣ በአዲሉስ፣ በጉራ … ደማችዉን ያፈሰሱለትን አረንጓኤ ቢጫ ቀይ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ሰማያዊ ኮከብ ካልተደረገበት የሚያስቀጣዉ ሕግ ፣ በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ላይ የተወሰደዉ ኢሰብአዊና ኢፍትሃዊ የጭካኔ እርምጃ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ በተቃዋሚውች ላይ በየወረዳዉና በየክልሉ የሚደርሰዉ ወከባ … ኢሕአዴግን ከሕዝብ ጋር የሚያጣሉ፣ ጥላቻን እንዲሰፋ የሚያደርጉ፣ ዜጎች የበለጠ ወደ ከረረ አቋም እንዲሄዱ የሚገፋፉ እንጂ ጠቅላይ ሚኒስተር መለስ ዜናዊ እንደ አጀንዳ እንደግፈዋለን ያሉትን የመግባባትንና የእርቅን መንፈስ የሚያመጡ አይደለም።

ስለሆነም ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን የምለዉ ነገር ቢኖር «ድርጅትዎት በብሄራዊ መግባባት የሚያምን ከሆነ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተናገሩትን በሥራ ይተርጉሙት» የሚል ነዉ።

ጦርነት ያላወጁትን፣ በሰላምና በሕጋዊ መልኩ የሚታገሉትን፣ ከኢሕአዴግ ጋር አብረዉ ለመሥራት የተዘጋጁትን፣ አገዛዙን እንደ«ጠላት» በሚቆጥሩ ሰዎች ፊት «ወያኔ ጠላት አይደለም» ብለዉ የተሟገቱትን ማጥቃት፣ መግደል፣ ማሰር፣ ማፈን እንዴት ተደርጎ ነዉ እርቅና ብሄራዊ መግባባትን ማምጣት የሚችለዉ ? የሰለማና የፍትህ ሴት የሆኑትን ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን ከስድስት ወራት በላይ በጨለማ ቤት ማሰር፣ ነገሮችን የበለጠ ያካርራል እንጂ እንዴት ተደርጎ ነዉ አገርን የሚጠቅመዉ ?

ተናዶ የኃይል እርምጃ መወሰድ፣ በበቀል መነሳሳት፣ ሰዉን ማዋረድ፣ ሰዉን መስደብ፣ ሰዉን መክሰስ በጣም ቀላል ነዉ። በአይናችን ላይ ትልቅ ምሰሶ እያለ የሌላዉን ጉዳፍ ማየት፣ የተገነባዉን ማፍረስ፣ አገርን ከድህነት ወደ ድህነት ማወረድ፣ ጠላቶችን ማፍራት፣ ሕዝብን ከሕዝብ መከፋፈል፣ ወንድምን ከወንድም ማጣላት አስቸጋሪ አይደለም።

ይሳቅ ራቢን እንዳደረጉት ጠላት የነበሩትን ወዳጅ ማድረግ፣ የፈረሰዉን መገንባት፣ አገርን ከድህነት ማውጣት፣ ችግሮችን በዉይይት መፍታት፣ የተጣሉትን ማስታረቅ፣ የተበተኑትን መሰብሰብ፣ ትችትና ወቀሳን በትህትና ተቀብሎ ስድብና አሉባልታን ደግሞ ንቆ ነገሮችን በትእግስት ማሳለፍ ግን እጅግ በጣም ከባድ ነገር ነዉ።

ስለሆነም አቶ መለስ ዜናዊንና ጓደኞቻቸዉን፣ አሁንም የቀናዉን መንገድ እንዲይዙና በፓርላማ እንደሰማነዉ ሁሉ በተግባር ለእርቅና ለብሄራዊ መግባባት መዘጋጀታቸዉን ለማሳየት ተጨባጭ ሥራዎችን ለመሥራት እንዲነሱ ጥሪ አቀርባለሁ።

ከነዚህም ከተጨባጭ ስራዎች መካከልም በቀዳሚነት፣ በዋናነትና በአስቸኳይ ትልቅ ሥራ ሊሰራበትና እልባት ማግኘት ያለበት ጉዳይ ቢኖር የወ/ት ብርቱካን እሥር ጉዳይ ነዉ።

ወ/ት ብርቱካን ቃሌ በሚለዉ ጽሁፋቸው ይቅርታ መጠየቃቸዉን በግልጽ አስቀምጠዋል።«በሽማግሌዎች የእርቅ ማግባቢያ መንፈስ መሰረት በፖለቲካ የተቀሰቀሰዉን ክስ ፖለቲካዊ እልባት ለመስጠት በማሰብ ለእርቅ ስል ከሌሎች የፓርቲዉ (ቅንጅት) መሪዎች ጋር ተስማምቼ ሰኔ 11 ቀን 1999 ዓ.ም በተጻፈዉ ሰነድ በሽማግሌዎች አማካኝነት ይቅርታ ጠይቄአለሁ። ይህ ብፈልግም ልለዉጠዉ የማልችለዉ ሐቅ ነዉ» ነበር ያሉት።

ስለሆነም አቶ መለስ ዜናዊ ለቢቢሲ ሃርድቶክ ጋዜጠኛ ለመግለጽ እንደሞከሩት ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ያጭበረበሩት ወይንም ያታለሉት አንድ ነገር የለም። «የይቅርታ ዉሳኔ ለይቀር ተባዩ ከደረሰና ተቀባይነት ካገኝ በኋላ የይቀርታ ዉሳኔ በማጭበርበር ወይም በማታለል የተገኘ መሆኑ ከተረጋገጠ የይቀርታ ዉሳኔዉ ዋጋ አይኖረዉም» የሚለዉና በጠቅላይ ሚኒስተር መለስ ዜናዊ የሚጠቀሰዉ የይቅርታ ሥነ ሥርዓት አዋጅ ቁጠር 395፣ አንቀጽ 16፣ ንኡስ አንቀጽም 2 ፣ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን በጭራሽ አይመለከትም። «ይቅርታ አልጠየኩም» ሳይሉ፣ የማይገናኝ ይህንን የሕግ አንቀጽ እንደ ሌጦ በመተርጎም፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ደጋፊዎች ያሏቸዉንም እኝህን የሰላም ሴት በግፍ ማሰር አሳዛኝና አሳፋሪ እንጂ በምንም አይነት መልኩ አገራዊ መግባባትን የሚፈጠር አይደለም።

ኢሕአዴጎች፣ ተቃዋሚዎች ሁላችንም ብሄራዊ መግባባትን በእዉነት ከፈለግን፣ በሁላችንም ዘንድ የልብ መሻት ካለ እንቆቅልሾቻችንን መፍተት ያችላል። ስለዚህ በትጋትና በቅንነት ወደ አንድነትና ወደ እርቅ ሁላችንም ልባችንን እናነሳሳ። ኢሕአዴግ በአስቸኳይ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በመፍታትና የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት ለብሄራዊ መግባባት ያለዉን ቁርጠኝነት በግልጽ ያሳይ። እንደ ኢሳቅ ራቢን ደፋርና ሰላምን የሚያበራክቱ እርምጃዎችን ይወሰድ።


Monday, July 06, 2009

 

ብርቱካንን ከማሰር አይነት ጎጂ ድርጊት መቼ ነዉ ኢሕአዴግ የሚገደበዉ ? ከድርጅቱ ደጋፊ


ግርማ ካሳ (muziky68@yahoo.com)

ሰኔ 29 ቀን 2001

አባ መላ በሚል ስም የሚታወቁትና አፍቃሪ-ኢሕአዴግ የሲቪሊቲ ፓልቶክ ክፍልን የሚያንቀሳቅሱ የገዢዉ ፓርቲ ደጋፊ (ምናልባትም ባለሥልጣን) አንድ ከፍተኛ የኢሕአዴግ አመራር አባላትን ሲጠይቁ ከተናገሩት የሚከተልዉ ይገኝበታል።

«አንዳንድ ጊዜ ከኢሕአዴግ በኩል፣ በዳያስፖራዉ የኢሕአዴግን ደጋፊዎች ሁሉ ሳይቀሩ፣ criticise የሚያደርጉት popular ያልሆኑ ነገሮችን ትወስዳላቹህ። አላስፈላጊ የሆነ። ለምሳሌ በቅርቡ በብርቱካን ሚደቅሳ ላይ የተወሰደዉ እርምጃ ምንም እንኳን ጥፋት አጥፍታለች ቢባልም ቴክኒካሊ፣ አስፈላጊ ያልሆነ confrontation ነዉ። ብዙ የምንሰራዉ፣ እንደ አገር የምንሰራዉ ብዙ ነገር አለ። በሕግ አንጻር ሁሉን ነገር እንደ ሌጦ መተርጎም የለብንም። ሌሎች moral values የሕዝብ አስተያየት የመሳሰሉ ነገሮችን ግምት ዉስጥ አስገብቶ ማየት ይገባል። የአንድ ጠንካራ መንግስት መለኪያዉ እርሱ ነዉ ብለን እናምናለን። ምን አልባት እነዚህን የመሳሰሉ ነገሮች፣ implication ያላቸዉን ጉዳዮች avoid ለማድረግ ኢሕአዴግ በኩል አንዳንድ ድክመት አለ። በሕዝብ ታዋቂ የሆኑ በጥሩም ሆነ በመጥፎ ተወዳጅነት ያላቸዉ የሙዚቃ ሰዉ ሊሆን ይችላል። ስፖርተኛ ሊሆን ይችላል። ወይም የፖለቲካ ሰዉ። በተለይ የብርቱካን ጉዳይ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ዉስጥ እርስዎም እንደሚያወቁት፣ የሴቶች ታጋዮች ሚና በጣም በጣም ትንሽ ነዉ። በተቃዋሚም እንኳን ብትሆን «በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ እታገላለሁ» ብላ የገባች እስከሆነች ድረስ፣ በአምጽ የሚታገሉትን ተቃዉመን፣ ጠመንጃ ከሻቢያ ጋር አንስተዉ ግለሰቦችን ለመግደል፣ ተቋሞችን ለማፍረስ፣ የሚንቀሳቀሱትንም እያወገዝን፣ በሰላም «አገሬ ዉስጥ ሕግና ሕገ መንግስት አለ። መንግስትን ፊት ለፊት እታገላለሁ» ብሎ የገባዉንም ኃይል እኩል treat ማድረግ የለብንም። በተለይ ሴት በመሆኗ፣ የልጅ እናትም በመሆኗ በኢትዮጵያ ዉስጥ የሴቶችን ሚና ከፍ ለማድረግ ከፍተኛ እምነት አለዉ ብዬ ስለማምን፣ ኢሕአዴግ በእንደዚህ አይነት ሰዎች ላይ የምትወስዱት እርምጃ በምንም መልክ defend ልናደርግ justify ልናደርግ እያቃተን ነዉ። ከእንደዚህ አይነት unpopular ድርጊት መቼ ነዉ ኢሕአዴግ የሚገደበዉ? ይሄን ጉዳይ በቅርቡ ለመፍታት የታሰበ ነገር አለ ወይ ?»


እኝህ ሰዉ፣ የሚደግፉት ፓርቲ ሕግን እንደሌጦ እየተረጎመ አላስፈላጊ ጎጂ ሥራዎችን እየሰራ እንደሆነ ነዉ የሚነግሩን። በተለይም በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ላይ የተወሰደዉ እርምጃ እንዳሳዘናቸዉ አበ መላ በድፍረት ገልጸዋል።

በዚች መጣጥፍ ሕግን እንደሌጦ የመተርጉሙ ጉዳይ ላይ አንዳንድ ሃሳቦች ለመስጠት እሞክራለሁ።በቅርቡ አቶ መለስ ዜናዊ ለአገር ዉስጥ ጋዜጦኞች በሰጡት ቃለ መጠይቅ ሰፋ ባለ ሁኔታ በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ጉዳይ ላይ ሃተታ አቅርበዋል። ከኢሕአዴግ ደጋፊዎችና ከሌሎች፣ ወ/ት ብርቱካን ሚድቀሳ እንዲፈቱ የሚጥይቁ ብዙ ደብዳቤዎች እንደደረሳቸዉና እርሳቸዉም የወ/ት ብርቱካን መታሰር እንዳሳዘናቸዉ በቃለ መጠይቁ ወቅት ገልጸዋል።

«ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ይፈቱ» ብለዉ ከሚጠይቁት ደብዳቤዎች መካከል አንዳንዶቹ ሰብአዊነትን ከግምት ዉስጥ በማስገባት፣ ሌሎች ደግሞ «ኢሕአዴግን ይጎዳል፣ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታዉን ወደ ኋላ ይጎትታል» በሚል እንደሆነ አቶ መለስ አስረድተዉ፣ የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ጉዳይ ግን የሕግ ጉዳይ በመሆኑ ምንም ማድረግ እንዳልተቻለ ነበር የተናገሩት።

ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ይቅርታ ካገኙ በኋላ ይቅርታ አልጠየኩም እንዳሉ፣ ይቅርታ አልጠየኩም በማለታቸዉ ደግሞ ከዚህ በፊት ይቅርታ ሲሰጣቸዉ አጭበርብረዉ ነበር ማለት እንደሚቻል፣ በማጭበርበር የተገኘ ይቅርታ ደግሞ በሕጉ መሰረት መሰረዝ እንዳለበት ነበር አቶ መለስ የተናገሩት። ይህንን ሲናገሩ ፡

«የይቅርታ ዉሳኔ ለይቅር ተባዩ ከደረሰና ተቀባይነት ካገኘ በኋላ የይቅርታ ዉሳኔ በማጭበርበር ወይም በማታለል የተገኘ መሆኑ ከተረጋገጠ የይቅርታ ዉሳኔዉ ዋጋ አይኖረዉም

የሚለዉን የይቅርታ ሥነ ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 395፣ አንቀጽ 16 ፣ንኡስ አንቀጽ 2 አስበዉ እንደሆነ እገምታለሁ።

እዚህ ላይ ነዉ እንግዲህ ሁኔታዎችን ያላገናዘበ፣ የአገርን ጥቅም ከግምት ዉስጥ ያላስገባ፣ በይቅርታ ሥነ ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 395 ዉስጥ ያሉትን ሌሎች አንቀጾችን ሁሉ ያልተመለከተ በነጠላዉ፣ አባ መላ እንዳሉት፣ እንደሌጦ የሆነ የሕግ ትርጓሜ ነዉ የምናየዉ።በመጀመሪያ ደረጃ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ «ይቅርታ አልጠየኩም” አላሉም። ቃሌ በሚለዉ ጽሁፋቸው ለሁለተኛ ጊዜ ከመታሰራቸዉ ከአንድ ቀን በፊት፣ ይቅርታ መጠየቃቸዉን በግልጽ አስቀምጠዋል።

«በሽማግሌዎች የእርቅ ማግባቢያ መንፈስ መሰረት በፖለቲካ የተቀሰቀሰዉን ክስ ፖለቲካዊ እልባት ለመስጠት በማሰብ ለእርቅ ስል ከሌሎች የፓርቲዉ (ቅንጅት) መሪዎች ጋር ተስማምቼ ሰኔ 11 ቀን 1999 ዓ.ም በተጻፈዉ ሰነድ በሽማግሌዎች አማካኝነት ይቅርታ ጠይቄአለሁ። ይህ ብፈልግም ልለዉጠዉ የማልችለዉ ሐቅ ነዉ»


ነበር ያሉት።

በሁለተኛ ደረጃ በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ላይ የተወሰደዉ እርምጃ የይቅርታ ሕጉን አላማ ያላንጸባረቀ እርምጃ ተደርጎ የሚወሰድ ነዉ። የይቅርታ ሥነ ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 395 አንቀጽ 11 የይቅርታው ዓላማ ምን እንደሆነ በማያሻማና በማያከራክር መልኩ በግልጽ አስቀምጦታል። አንቀጽ 11 እንዲህ ያላል ፡

“የይቅርታ አላማ የሕዝብን ደህንነትና ጥቅም ማስከበር ነዉ” ።

በአንቀጽ 11 መሰረት በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ላይ የተወሰደዉ እርምጃ ቢመዘን ምን ያህል የሕዝብን ደህንነትና የአገርን ጥቅም ያስከብራል የሚል ጥያቄን ብናነሳ የኢትዮጵያን ሁኔታ የሚከታተል ማንኛዉም ሰዉ የሚመለሰዉ ነዉ።

ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በኢትዮጵያ ዉስጥ ያለዉን የአገሪቱን ሕግ በመከተል፣ ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ እያደረጉ የነበሩ ሴት ናቸዉ። በሕግ የተመዘገበ የአንድ አብይ የፖለቲካ ፓርቲ፣ አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ሊቀመንበር ናቸዉ። በ1999 ዓ.ም ማለቂያ ወቅት ከቃሊቲ እሥር ቤት ከተፈቱ ጊዜ ጀምሮ ለሁለተኛ ጊዜ እሥር ቤት እስከገበቡበት ጊዜ ድረስ የተከሰሱበት አንዳች ወንጀል የለም። የርሳቸዉ መታሰር በምንም መልኩ የአገርን ደህንነትና ጥቅም ከማስከበር አንጻር የሚያመጣዉ አዋንታዊ ድርሻ የለም።

ይልቅስ የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ መታሰር ዜጎች በሰላማዊ ትግል ላይ ያላቸዉ ተስፋ እንዲሞነሙን አድርጓል። ብዙዎች ተስፋ ከመቁረጣቸዉ የተነሳ ወደ ጠመንጃ ትግል ፊታቸዉን እያዞሩ ነዉ። በኢትዮጵያዉያን ዘንድ መከፋፈሉና ጥላቻዉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ሲሆን ድህነትንና እንደ አልሻባብ ያሉ ሽብርተኞችን በጋራ እንዳንመክት መተማመንና አንድነት ከመካከላችን እየጠፋ ነዉ።

«ሕግ እንደሌጦ መተርጎም ቆሞ፣ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በአስቸኳይ ይፈቱ። የፖለቲካ ምህዳሩን ይስፋ» እላለሁኝ። አባ መላ ያሉትን በመጥቀስ ኢሕአዴግ ከጎጂ ድርጊቶች ለራሱ፣ ለሕዝብ፣ ለአገርና ለተተኪዉ ትዉልድ ሲል እንዲቆጠብ እጠይቃለሁ።

በጋራ በፍቅር አገቻችንን አሁን ካለችበት የድህነት አዝቅት፣ የወርደት ካባ እናወጣት።


http://peacewithkinijit.tripod.com/sibhat.wma

This page is powered by Blogger. Isn't yours?