Thursday, June 25, 2009

 

እኛም የዲሞክራሲ ጀግኖች አሉን !

ግርማ ካሳ (muziky68@yahoo.com)

















ግርማ ካሳ (muziky68@yahoo.com)

ሰኔ 29 ቀን 2001

ኔዳ አጋ ሱልጣን ትባላለች። በቅርቡ የተደረገዉን የምርጫ መጭበርበር በተመለከተ በኢራን በተደረገዉ ሰላማዊ ሰልፍ ከደህንነት አባላት በተተኮሰ ጥይት የተገደለች ናት። ከቤቷ ስትወጣ የወጣችዉ ድምጿ እንዲከበርላት፣ የሰብዓዊ መብቷ እንዲረጋገጥ በሰላም ነበር። በሕይወቷ ማከናወን የምትፈልጋቸዉ ብዙ እቅዶች ይኖሯታል። ነገር ግን እቅዶቿን ሁሉ ትታ ወደቀች። ተገደለች።

ኔዳ የዲሞክራሲ ምልክት ሆና በአለም ሁሉ ስለእርሷ እየተነገረ ነዉ። በኢራን የዲሞክራሲ ታጋዮች ዘንድ፣ በሥጋዋ ከዚህ አለም ብትለይም፣ በኢራን የዲሞክራሲ ትግል ታሪክ ዉስጥ ግን ልዩ ቦታ ይዛለች። የሞተችበት አላማም በሕዝቡ ዉስጥ ማእከል ቦታ ይዞ እየተቀጣጠለ ነዉ።

እኛ አገር ተመሳሳይ ሁኔታ ከአራት አመታት በፊት አይተናል። አሁን በሥልጣን ላይ ያለዉ የኢሕአዴግ መንግስት በምርጫ ከፍተኛ ሽንፈት ሲደርስበት፣ ኮረጆ መቀያየር ጀመረ። ሳያሸንፍ አሸንፊያለሁ ብሎ አወጀ። የምርጫዉን መጭበርበር፣ በኢራን አሁን እየተደረገ እንዳለዉ፣ ሕዝብ ሰላማዊ ሰልፍ በመዉጣት ተቃወመ። በአቶ መለስ ዜናዊ የሚመራዉ የአጋዚ ጦርና የፌደራል ፖሊሲ ትልቅ ጭካኔ የተሞላበት የኃይል እርምጃ ወሰዱ። በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎችን ገደሉ።

የዚያን ጊዜ ነበር የአሥራ ስድስት አመቷ ወጣት፣ የኛ «ኔዳ» የሆነችዉ፣ ሽብሬ ደሳለኝ ለዲሞክራሲና ለነጻነት ስትል የተገደለቸዉ። አለም ስለርሷ አልዘገበም። ሲኤንዔን፣ ቢቢሲ ዋሺንግተን ፖስትና ኑዮርክ ታይምስ ፎቶዎቿን አላወጡም። የምእራባዉያን አገሮች ተቃዉሟቸዉን አላሰሙም። ብዙዎች አያዉቋትም። ነገር ግን እኛ እናዉቃታለን። በኛ ዘንድ ግን የተረሳች አይደለችም።

ይሄን ጊዜ ሽብሬ ደሳለኝ ሃያ አመት ይሆናት ነበር። ምናልባትም የዮኒቨርሲቲ ተማሪ ልትሆን ትችል ነበር።

ገዳዮቿ ሊረሱ ይችላሉ። ከአራት አመት በፊት የሰሩትን ግፎች ከዚያ በኋላ እየደጋገሙ ስለፈጸሙ ብዙ ያስታዉሱታል ብዬ አላስብም። ነገር ግን አንድ የምናዉቀዉ ነገር አለ። ሽብሬ ደሳለኝ መቼም ቢሆን አትረሳም። እስከ አሁን ድረስ የሕሊና ጆሮ ላለዉ ሰዉ፣ የፈሰሰዉ ደሟ ሲጮህ ይሰማል። አሁንም ሽብሬ ደሳለኝ ትጣራለች። አሁንም መልእክቶቿ እየደረሱን ነዉ።

«ትግሉን ተቀላቀሉ። በአገራቹህ ጉዳይ ላይ ባይተዋር አትሆኑ። ከሌሎች ህዝቦች ተማሩ። ሌላዉ ሲጠቃ ዝም የሚል የፈሪ ባህልን አስወግዱ። እኛ ደማችንን ያፈሰስንበትን አላማ ከግቡ አድርሱት።» ትለናለች።

እነ በርቱካን ሚድቅሳ የሽብሬን ጥሪ ተቀብለዉ የጨካኞችን ግፍ እየተቀበሉ ነዉ። ለእዉነትና ለሐቅ በመቆም፣ ማስፈራሪያንና ዛቻን በመናቅ እርሳቸዉን ሰውተዉ ደረታቸዉን ለጥይት አሳልፈዉ ሰጥተዋል።

እኛስ ? መልሳችን ምንድን ነዉ ?

Comments: Post a Comment



<< Home

This page is powered by Blogger. Isn't yours?