Friday, June 19, 2009

 

አቶ ስብሐት ነጋ በብርቱካን መታሰር ላይ

ሰኔ 12 ቀን 2001

የዘመኑ ቴክሎሎጂ ከፈጠራቸዉ የመገናኛና የመወያያ መድረኮች አንዱ ፓልቶክ ነዉ። በኢትዮጵያዉያን የሚንቀሳቀሱ በርጋታ ፓልቶክ ክፍሎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበዙ ነዉ። ከነዚህ ፓልቶክ ክፍሎች መካከል የኢትዮ ሲቪሊቲ ፓልቶክ ክፍል አንዱ ነው። ይህ ክፍል ከሌሎች ክፍሎች የሚለየዉ ነገር ቢኖር 95 በመቶ አፍቃሪ ኢሕአዴጎችን ያሰባሰበ መሁኑ ነዉ። የክፍሉ አስተባባሪዎች ጠንካራ የገዢዉ ፓርቲ ደጋፊዎች ምናልባትም በሥርዓቱ ዉስጥ ትልቅ ቦታ ያላቸዉም ሊሆኑም ይችላሉ። በተለያዩ መጣጥፍት ለኢሕአዴግ አባላት፣ ፓርቲያቸዉ ከሕዝብ እንዲታረቅና ወደ ቀናዉ መንገድ እንዲመለስ ቀርቦላቸዋል። ከነርሱ ዉስጥ ጥሩ ልብ ያላቸዉ ሰዎች አይለዉ ወጥተዉ መልካም ነገር ሊፈጠር ይችላል የሚል ትንሽ ብትሆንና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየመነመነች ብትመጣም ተስፋ ያለን ጥቂት አይደለንም።

በዚህ መንፈስ የኢሕአዴግ ደጋፊዎችን ለማነጋገር፣ ዉስጥ ዉስጡን ትልቅ ግፊት ማድረግ እንዳለባቸዉ ለማሳሰብ ወደዚህ የሲቪሊቲ አፍቃሪ ኢሕአዴግ ፓልቶክ ክፍል ገባሁ። በኔና በሚሊዮን በሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉያን ዘንድ ትልቁና አንገብጋቢ ጉዳይ የሆነዉን በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ላይ እየተፈጸመ ያለዉን ኢሰብዓዊና ኢፍትሃዊ ግፍን በተመለከተ ሕሊና ያለዉ ሰዉ በሙሉ፣ ኢሕአዴግን እንደግፋለን የሚሉ ሳይቀር ድምጻቸዉን ማሰማት እንዳለባቸዉ አሳሰብኩኝ።
በክፍሉ ያሉ በርካታ የኢሕአዴግ ደጋፊዎች የወ/ት ብርቱካን መታሰር እንዳሳዘናቸዉና አጥብቀዉ እንደተቃወሙት፣ ለአመራር አባላቱም በግልጽ ያላቸዉን ትልቅ ተቃዉሞ እንዳቀረቡ ፣ ወደፊት ወ/ት ብርቱካን እንድትፈታ ጥረታቸዉ እንደሚቀጥሉ አሳወቁኝ። ምሳሌም እንዲሆን አቶ ስብሀት ነጋ በክፍሉ ቀርበዉ ቃለ መጠይቅ በተደረገላቸዉ ጊዜ በጣም ጠንካራ በሆነ መልኩ የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ጉዳይ እንደተነሳ ነገሩኝ። ቃለ መጠይቁን እንዳዳምጥ የኢንተርኔት አድራሻዉን አሳወቁኝ።

ጊዜም አልፈጀብኝም ከአቶ ስብሀት ነጋ ጋር የተደረገዉን ረጅም ቃለ መጠይቅ አዳመጥኩኝ። በቃለ መጠይቁ አብዛኛዉ በአሜሪካን ድምጻ ሬዲዪ አቶ ስብሀት ከተናገሩት ይልተለየ ነበር። ሕግ የበላይ መሆን እንዳለበት፣ ሐገ መንግስቱ መከበር እንዳለበት፣ ሕገ መንግስቱ እንደብርቅዬ ልንጠብቀዉ የሚገባ እንደሆነ አቶ ስብሀት አጠንክረዉ ተናገሩ። ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በተመለከተ አባ መላ በሚል ስያሜ የሚታወቀዉ የክፍሉ ዋና አስተባባሪ የሚከተለዉን ጥያቄ አቀረበ። «አንዳንድ ጊዜ ከኢሕአዴግ በኩል፣ በዳያስፖራዉ የኢሕአዴግን ደጋፊዎች ሁሉ ሳይቀሩ፣ criticise የሚያደርጉት popular ያልሆኑ ነገሮችን ትወስዳላቹህ። አላስፈላጊ የሆነ። ለምሳሌ በቅርቡ በብርቱካን ሚደቅሳ ላይ የተወሰደዉ እርምጃ ምንም እንኳን ጥፋት አጥፍታለች ቢባልም ቴክኒካሊ፣ አስፈላጊ ያልሆነ confrontation ነዉ። ብዙ የምንሰራዉ፣ እንደ አገር የምንሰራዉ ብዙ ነገር አለ። በሕግ አንጻር ሁሉን ነገር እንደ ሌጦ መተርጎም የለብንም። ሌሎች moral values የሕዝብ አስተያየት የመሳሰሉ ነገሮችን ግምት ዉስጥ አስገብቶ ማየት ይገባል። የአንድ ጠንካራ መንግስት መለኪያዉ እርሱ ነዉ ብለን እናምናለን። ምን አልባት እነዚህን የመሳሰሉ ነገሮች፣ implication ያላቸዉን ጉዳዮች avoid ለማድረግ ኢሕአዴግ በኩል አንዳንድ ድክመት አለ። በሕዝብ ታዋቂ የሆኑ በጥሩም ሆነ በመጥፎ ተወዳጅነት ያላቸዉ የሙዚቃ ሰዉ ሊሆን ይችላል። ስፖርተኛ ሊሆን ይችላል። ወይም የፖለቲካ ሰዉ። በተለይ የብርቱካን ጉዳይ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ዉስጥ እርስዎም እንደሚያወቁት፣ የሴቶች ታጋዮች ሚና በጣም በጣም ትንሽ ነዉ። በተቃዋሚም እንኳን ብትሆን «በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ እታገላለሁ» ብላ የገባች እስከሆነች ድረስ፣ በአምጽ የሚታገሉትን ተቃዉመን፣ ጠመንጃ ከሻቢያ ጋር አንስተዉ ግለሰቦችን ለመግደል፣ ተቋሞችን ለማፍረስ፣ የሚንቀሳቀሱትንም እያወገዝን፣ በሰላም «አገሬ ዉስጥ ሕግና ሕገ መንግስት አለ። መንግስትን ፊት ለፊት እታገላለሁ» ብሎ የገባዉንም ኃይል እኩል treat ማድረግ የለብንም። በተለይ ሴት በመሆኗ፣ የልጅ እናትም በመሆኗ በኢትዮጵያ ዉስጥ የሴቶችን ሚና ከፍ ለማድረግ ከፍተኛ እምነት አለዉ ብዬ ስለማምን፣ ኢሕአዴግ በእንደዚህ አይነት ሰዎች ላይ የምትወስዱት እርምጃ በምንም መልክ defend ልናደርግ justify ልናደርግ እያቃተን ነዉ። ከእንደዚህ አይነት unpopular ድርጊት መቼ ነዉ ኢሕአዴግ የሚገደበዉ? ይሄን ጉዳይ በቅርቡ ለመፍታት የታሰበ ነገር አለ ወይ ?»

እዚህ ላይ አባ መላ ለመናገር እንደሞከረዉ ገዢዉ ፓርቲ በወ/ት ብርቱካን ላይ የወሰደዉ እርምጃ በምንም መልኩ ሚዛን የማይደፋ፣ የራሳቸዉን ደጋፊዎች እንኳን ማሳመን ያልቻለ ትልቅ ስህተት እንደሆነ እናያለን።

በመርህ ደረጃ ማንም ሰዉ ለሕግ መገዛት እንዳለበትና ከሕግ በላይ ሊሆን እንደማይችል አቶ ስብሃት ከተናገሩ በኋላ የሚከተለዉን ነበር ያሉት፡

«ማንኛዉ እርምጃ ሲወሰድ በጥልቀት የማንኛዉም እርምጃ መነሻዉና መድረሻው ጠቃሚነቱና ጉዳቱ መታወቅ አለበት። ማንኛዉም እርምጃ ጉዳት የሌለዉ የለም። እኔ ወደ ቤቴ ከዚህ ስሄድ risk አለዉ። ግን አልሄድም ልል አልችልም። መሄድ አለብኝ። ስለዚህ risk የሌለዉ ነገር የለም።ጉዳቱን ጥቅሙ የትኛዉ ይበለጣል ነዉ። ብርቱክንን ማሰር ጉዳት አለዉ። ጥቅሙስ ? ጉዳቱና ጥቁምን ማስረዳት አለመቻላችን፣ አለማስተማራችን፣ አለማሳወቃችን፣ ከመደረጉ በፊትም ከተደረገም በኋላም ጉድለታችን ይመስለኛል። ከዚህ ባሻገር «አሁን ምን እየታሰበ ነዉ» ላልለከዉ እኔ በአገር ጥቅም ላይ compromise እርቅ መምጣት የለበትም። ማንኛዉም ሰዉ ከጥፋቱ በላይ መቀጣት የለበትም። ከጥፋቱ በታችም መቀጣት የለበትም። የፈጸመዉን ቅጣት የሚመጥን ቅጣት ማግኘት አለበት። ስለዚህ ብርቱክናም የፈጸመችዉን ጉዳት የሚመጥን ቅጣት ማግኘት አለባት። ከዚያ በታች ሳይሆን ከዚያ በላይ ሳይሆን። ምንድን ነዉ ጥፍቷ ? ከሰላም ጋር የተያያዘ ነዉ ? ምንድን ነዉ የተከሰሰችበት አንቀጽ ? አላዉቀዉም ! አንቀጹ ምን ያስቀጣል ? አላዉቀዉም። ግን ፍትሃዊና ቀልጣፋ ፍርድ ግን እንድታገኝ እመኝላታለሁ።»

እዚህ ላይ አቶ ስብሀት «ብርቱካን የተከሰሰችበትን ጥፋት አላዉቀዉም» ነዉ የሚሉን። አቶ ስብሀት ብርቱካን ለምን እንደታሰረች ያጡታል ብዬ አላምንም። ነገር ግን ወ/ት ብርቱካን ላይ የደረሰዉ ግፍ አተፋች የተባለዉን በጭራሽ የሚመጥን እንዳልሆነ፣ አተፋች የተባለዉም በሕግ ፊት ሚዛን የሚደፋ እንዳልሆነ የተረዱና የሚያምኑ ይመስለኛል። በዚህም ምክንያት እንደ ኢሕአዴግ ከፍተኛ አመራር አባል እነ በረከት የሚመልሱትን መልስ ለመመለስ የከበዳቸዉና እንዲሁ በደፈናዉ «አላዉቅም» ብለዉ ማለፉን የመረጡ ይመስላል።

ከአንዳንድ ምንጮች ለመረዳት እንደተቻለዉ በኢሕአዴግ ዉስጥ በጣም አክራሪና ግትር ከሚባሉት መካከል አቶ ስብሀት ነጋ አንዱ ናቸዉ። እኝህ ሰዉ ከሁለት አመታት በፊት የቅንጅት መሪዎች መፈታት የለባቸዉ የሚል ጠንክራ አቋም የነበራቸዉ ሲሆን ለረጅም ዘመን የድርጅቱ መሪ እንደመሆናቸዉ ከበስተጀርባ ሆነዉ እንደ ቀድሞ የጣሊያን ማፊያ መሪዎች ብዙ ነገሮችን የሚያሽከረክሩ ናቸዉ የሚሉ ጥቂቶች አይደሉም። ከዚህ በፊት ባደረጉት ቃለ መጠይቅ «ቅንጅት ጠላት ነዉ» የሚል አሳፋሪና አሳዝኝ አባባል መጠቀማቸዉም ይታወሳል።

ኦዲዮዉንም ለማዳመጥ ከታች ያለዉ የኢንተርኔት አድራሻ ጋር ይሂዱ !

http://peacewithkinijit.tripod.com/sibhat.wma

Comments: Post a Comment



<< Home

This page is powered by Blogger. Isn't yours?