Wednesday, June 17, 2009

 

በቃሊቲ እሥር ቤት ሰሞኑን የተከሰተዉን አሳዝኝ ሁኔታ በተመለከተ - ግርማ ካሳ

ሰኔ 9 ቀን 2001

ቶርቸር (ሰቆቃ) ከአለም እንዲጠፋ የሚታገል የአለም አቀፍ የጸረ-ቶርቸርና የተጎጂዎች ደጋፊ ድርጅት፣ የአይምሮን ቶርቸር ሲተነትን፣ ረዘም ላለ ጊዜ በጨለማ ቤት ዉስጥ ማስቀመጥን፣ እንቅልፍ ማሳጣትን፣ መድፈርንና የመሳሰሉትን ከቶርቸር ዉስጥ ያስገባቸዋል። በእንደዚህ አይነት የአይምሮ ቶርቸር የሚያልፉ ሰዎች እራሳቸዉን እንዲጠሉ የሚያደርግና የሚቆይ ከፍተኛ የአይምሮ በሽታን እንደሚያመጣ ይናገራሉ።[1]

የለንደን ዪኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ከቤልግሬድ የሕክምና ኮለጅ ጋር በመተባበር 279 የቀድሞ እሥረኞችን በማነጋገር፣ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ መረጃዎችን ሰብስበዋል። በሰበሰቡትም መረጃ መሰረት የደረሱበት ድምዳሜ የአይምሮ ቶርቸር ከአካላዊ ቶርቸር በምንም እንደማይለይ የሚገልጽ ነበር። የአይምሮ ቶርቸርን እንደ አካላዊ ቶርቸር የሚያግድ አለማቀፋዊ ሕግ መዉጣት እንዳለበትም አሳስበዋል።[2]

እሲት ለትንሽ ጊዜ ከምናደርጋቸዉ እንቅስቃሴዎች ቆጠብ እንበል። አይኖቻችንን እንጨፍን። እራሳችንን ሁለት ሜትር በሁለት ሜትር ባለች ጠባብ ክፍል ዉስጥ እንየዉ። የምንተኛበት መኝታ በጣም ይቆረቁራል። ከመጨለሙ የተነሳ ብዙም አይታየንም። ከእንቅልፋችን ስንነሳ ጨለማ ነዉ። ወደ መኝታ ስንሄድ ጨለማ ነዉ። በቀዳዳ፣ ሕይወታችንን ለጊዜው የሚያቆይ አፍ ላይ የሚደረግ ይወረወርልናል። ተኝተንም ሳለ የወፎችን ጫጫታ ወይንም ሙዚቃ ወይንም የሰዎች ድምጽ ሳይሆን የአይጦችን ጭጭጭ የሚል ድምጽ ነዉ የምንሰማዉ። አንዳንዴም አይጦቹ በተኛንበት በላይችን ላይ ይበራሉ። መጽሃፍ ማንበብ አንችልም። ሬዲዮ መስማት አንችልም። ቴሌቭዥኑንማ እርሱት።

መልካችንን የምናይበት መስታወት የለም። መስታወትም ቢኖር ጨለማዉ መስታወቱን ተራ ግድግዳ አድርጎታል። ቢገድሉን ወይንም ቢደበድቡን ደስ ይላቸዉ ነበር። ግን የምእራቡን አለም ይፈራሉ። ስለዚህም በቀላቸዉን በሌላ ነገር ይወጡታል። አዉቀዉ ትናንሽ ጉንዳንና ቱሃን ይለቁብናል። ጉንዳኖቹና ቱሃኖቹ ሰዉነታችንን ይነክሳሉ። አንዱን ከእጃችን ስናራግፍ አንዱ በእግራችን ይመጣል።ሰዉነታችን ይላላጣል። «የሐኪም ያለህ» ብንል የሚሰማ የለም። ብናለቅስ የሚሰማ የለም። ግድግዳዉን ብንደበድብ የሚሰማ የለም። ብንለምን ፣ «እባካችህ በእመብርሃን ፣ በመድሃኔ አለም፣ በጊዮርጊስ ፣ በአላህ» ብንል የሚሰማ የለም።

ለአንድ ቀን ብቻ አይደለም። ከአንድ ቀን አልፎ ለሁለት ቀናት …. ከዚያም ለሶስት ቀናት ..ለአሥር ቀናት …. ለሃያ ቀናት …. ቀኑ እየተራዘመ መጣ። ቀናት መቁጠራችንን ቀጠልን። አንድ መቶ ስድሳት አምስት ላይ ደረስን። እሲቲ እናስብ እራሳችንን ! አናብድም ? አይምሯችንን አንስተም? እራሳችንን አንጠላም? አንታመም ?

በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ላይ የደረሰዉ እንግዲህ ይሄ ነዉ። በእጇ ጠመንጃ አልያዘችም። ሁለንም የምትወድ ናት። ፍቅርን ፍትህን አንድነት ነዉ የሰበከችዉ። በምቾት ተሰዳ በምእራቡ አለም መኖር ስትችል አገሬንና ህዝቤን ብላ ለአገሯ ለመታገል የወሰነች አገር ወዳድ ሴት ናት።

ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ከታህሳስ 20 2001 ዓ.ም ጀመሮ እስከ ሰኔ 7 ቀን 2001 ድረስ በግፍና በጭካኔ በጠባብ ጨለማ ክፍል ዉስጥ፣ ከሰዉ እንዳትገናኝ ተደርጎ ከጉንዳንና ከአይጦች ጋር ነዉ የምትወለዉና የምታደረዉ። ፍርድ ቤት ትእዛዝ ቢሰጥም ከዘመድ ወዳጅ፣ ከሃኪም ከጠበቃዋ ጋር እንዳትገናኝ ታግዳለች።

ማክሰኞ ሰኔ 4 2001 ዓ.ም ትልቅ አስደንጋጫ ክስተት ተፈጠረ። የስድስት ወር ቶርቸር የወለደዉ እጅግ በጣም አሳሳቢ ነገር ነበር።በርጋታዋና በብርታቷ የምትታወቀዉ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ከታሰረችበት አካባቢ ከፍተኛ ጩኸት እንደተሰማ አቡጊዳ ዘገበ። ለምን ወ/ት ብርቱካን እንደጮኸች እስከአሁን ማወቅ አልተቻለም። ከሰዉ እንዳትገናኝ አድርገዉ ምን እያደረጓት እንደሆነ እግዚአብሄር ነዉ የሚያወቀዉ። [3]

የመጀመሪያዉ አላማቸዉ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ እንድትል የሚፈልጉትን ብላ የፖለቲካ ተቀባይነት እንድታጣ ለማድረግና ትግሉን መሪ አልባ ለማሰኘት ነበር። አስፈራሯት። ዛቱባት። እርሷ ግን ናቀቻቸዉ። ለነርሱ ዉሸት እንደማትንበረከክ አሳየቻቸዉ።

እነርሱም በእልህና በጭካኔ መጡባት። «እንግዲያወስ በፈቃዷ ለኛ ፈቃድ ካልተገዛች፣ ቶርቸር አድርገን መንፈሷን ሰባብረን ዋጋ ቢስ እናደርጋታለን! እናሳብዳታለን !» ብለዉ ተነሱ። ብዙ ነፍሳት በገደለ ነፍሰ ገዳይ እንኳን ያልተፈጸመ በደል አደረሱባት። ለስደት ወር በጨለማ ቤት ዉስጥ በግፍ አስቀመጧት።

አቡጊዳ እንደዘገበዉ የማረሚያ ቤቱ ሃላፊዎች በማንም ሰዉ ላይ እንደዚያ ተደርጎ እንደማያዉቅ፣ በወ/ት ብርቱካን ላይ የሚደረገዉ ግፍ ከላይ በመመሪያና በትእዛዝ የመጣ እንደሆነ ይናገራሉ። (ከአራት ኪሎ ማለት ነዉ)

ለመሆኑ አራት ኪሎ የተቀመጡት ሰዎች (ሰዎች ልበላቸዉና) ይሄ ሁሉ ግፍ በዚች ሴት ላይ እንዲደርስ የሚፈቅዱት ምን ወንጀሏ ብትሰራ ነዉ ? «ወያኔ ጠላት አይደለም» ማለቷ ነዉ ወንጀሏ? ሰላማዊና ሕጋዊ ትግል ማድረጓ ነዉ ወንጀሏ? አገሯን ለቃ በስደት አለመኖሯ ነዉ ወንጀሏ?

«ለሕግ የቆምን ነን። ሕግ መከበር አለበት» ይሉናል። የትኛዉ ሕግ ? ሕግን ቢያወቁ ኖሮማ የፍርድ ቤትን ዉሳኔ ባከበሩ ነበር ? ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በጠበቃዎቻቸዉና በሃኪሞቻቸዉ በወዳጆቻቸዉ እንዲጎበኙም በፈቀዱ ነበር። ይቅርታዉን ከመሰረዛቸዉ በፊትም ሕጉ እንደሚያዘዉ፣ በጽሁፍ ምክንያታቸዉን ያሳዉቁና ለወ/ት ብርቱካንም፣ ምላሽ እንድትሰጥ፣ የሃያ ቀናት ጊዜ ይሰጡ ነበር።

የሕወሃቱ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ ለቢቢሲዉ ሃርቶክ ጋዜጠኛ ስለወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ተጠይቀዉ ሲመልሱ “ከተፈታች በኋላ ይቅርታ አልጠየኩም አለች። ያ ማለት ይቅርታ ያገኘቸዉ በማጭበርበር ነበር ማለት ነዉ። ስለዚህ በሕጋችን መሰረት በማጭበርበር የተገኘ ይቅርታ ወዲያዉኑ መሰረዝ አለበት” ነበር ያሉት።

“የይቅርታ ዉሳኔ ለይቅር ተባዩ ከደረሰና ተቀባይነት ካገኘ በኋላ የይቅርታ ዉሳኔ በማጭበርበር ወይም በማታለል የተገኘ መሆኑ ከተረጋገጠ የይቅርታ ዉሳኔዉ ዋጋ አይኖረዉም”[4] የሚለዉን በይቅርታ ስነ-ስርዓት አዋጅ ቁጥር 395፣ አንቀጽ 16፣ ንኡስ አንቀጽ 2 አስበዉ ይመስለኛል አቶ መለስ ይህ አይነት መልስ የሰጡት።

አዲስ አድማስ በሚባለዉ አገር ዉስጥ በሚታተም ጋዜጣ በይፋ በወጣዉ ጽሁፏ፣ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ስትጽፍ “ በሽማግሌዎቹም የእርቅ ማግባቢያ መንፈስ መሰረት በፖለቲካ የተቀሰቀሰዉን ክስ ፖለቲካዊ እልባት ለመስጠት በማሰብ ለእርቅ ስል ከሌሎች የፓርቲዉ መሪዎች ጋር ተስማምቼ ሰኔ 11 ቀን 1999 ዓ.ም በተጻፈዉ ሰነድ በሽማግሌዎች አማካኝነት ይቅርታ ጠይቂያለሁ። ይህ ብፈልግም ልለዉጠዉ የማልችለዉ ሐቅ ነዉ» ነበር ያለችዉ።[5]

እንግዲህ እዚህ ላይ የምናየዉ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በግልጽ «ይቅርታ ጠይቂያለሁ» እንዳለች ነዉ። ታዲያ አቶ መለስ ዜናዊ ከየት አምጥተዉ ነዉ «ይቅርታ አልጠየኩም አለች» እያሉ የሚናገሩት? የቱ ላይ ነዉ ወ/ት ብርቱካን ያጭበረበረችዉ ? ምንድን ነዉ ያታለለችዉ ? ምኑ ነዉ ጥፋቷ እንደዚህ ኢሰብአዊና አረመኒያዊ ግፍ ድርጅታቸዉ በዚች ሴት ላይ የሚያወርድበት ?

ዋሺንግተን ፖስት እንደዘገበዉ ወይዘሪት ብርቱካንን ጨምሮ የቅንጅት መሪዎች፣ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎችና ጋዜጠኞች በአገር ሽምግልና መሰረት ይቅርታ ጠይቀዉ በተፈቱ ጊዜ አቶ መለስ ዜናዊ የተናገሩት አባባል ነበር። «ይቅርታዉ ሙሉ ነዉ። ሕግን እስካከበሩ ድረስ ለመምረጥና ለመመረጥ ይችላሉ። ያለፈዉን ትተን፣ ወደኋላ ሳንመለስ ወደፊት ነዉ ማየት ያለብን» [6]ነበር ያሉት። ታዲያ «ወደ ኋላ አንመለስ። ያለፈዉን እንተዉ» ብለዉን እራሳቸዉ ግን ወደ ኋላ ተመልሰዉ «ይቅርታ ጠይቂያለሁ» ያለችዉን ሴት «ይቅርታ አልጠየኩም ብላለች» ብለዉ እንደነፍሰ ገዳይ ድርጅታቸዉ ማሰቃየቱ ምን ይባላል ? «

«ሕግን እስካከበሩ ድረስ» ድረስ ነበር ያሉት አቶ መለስ ዜናዊ። ታዲያ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የትኛዉን ሕግ ነዉ የጣሰችዉ ? ጠመንጃ አንስታ ሰዉ ገደለች? ወይንም የሕዝብን ገንዘብ መዝብራ ገንዝብ ወደ ዉጭ አሸሸች? ወይስ ጉቦ ተቀብላ ባገኘችዉና ባጠራቀመችዉ ገንዘብ አሜሪካ አገር ቤት ሰራች ? የቱ ነዉ ወንጀሏ ለዚህ ሁሉ ግፍ የዳረጋት ?

እንግዲህ አገር ፍረድ ! አሁን ያለዉን አገዛዝ እንደግፋለን የምትሉ፣ ልብና አይምሮ ያላቹህ ሁሉ ፍረዱ ! እንስሳዉና አዉሬዉስ እንስሳና አወሬ ነዉ። «ሰዉ ነን። እናስባለን፣ እናገናዝባለን» የምትሉ ሁሉ ፍረዱ ! የዚች ሴት ጥፋት ምንድን ነዉ ? እንደዚህ ቶርቸር የምትደረግበት ምክንያቱ ምንድን ነዉ ?

ይሄን ያህል ጭካኔ በሌላ ወገናችን ላይ እስክናደርስ ድርስ እንደዚህ አዉሬ የሚያደርገንስ ነገር ምንድን ነው ? ምን ይሻለን ይሆን ባካችሁ ? ለምንድን ነዉ እንዲህ የምንጨካከነዉ ? ለምንድን ነዉ አንዱ ሲጠቃ ሌላዉ ዝም ብሎ የሚመለከተዉ? ለምንድን ነዉ አንዱ ደብድብ ሲል ሌላዉ እሺ ብሎ የሚታዘዘዉ ? ምንድን ነዉ እንደዚህ ሕሊና ቢሶች ያደረገን ?

ኧረ አንተ ደጉ መድሃኔአለም ኢየሱስ ክርስቶስ በቃቹህ በለን ! እባክህን እኛም እንደሌሎቹ ሕዝቦች እንደታደሉት፣ ለተጠቁት የምንቆም፣ ለድሃ አደጉና ለመበለቲቶች የምንሟገት፣ የወደቀዉን የምናነሳ፣ የተሰበረዉን የምንጠግን፣ ክፋትንና ጭካኔ ቶርቸርን የምንጸየፍና የምንቃወም እዉነተኞች አድርገን !!! ብርቱካን ሚደቅሳንም አስባት ! ባላችበት ቦታ ኃይልህና ብርታትህ ጸጋህና ጥበቃህ አይለያት!





[1] http://www.tassc.org/index.php?sn=78
[2] http://www.abc.net.au/science/news/stories/2007/1864094.htm
[3] http://www.abugidainfo.com/?p=9813
[4] http://www.fsc.gov.et/Negarit%20Gazeta/Gazeta-1996/Proc%20No.%20395-2004%20Procedure%20of%20Pardon.pdf
[5] http://n.b5z.net/i/u/6142638/i/birtukan_1_.pdf
[6] http://www.washingtonpost.com/wp-dyn/content/article/2007/07/20/AR2007072000454.html

Comments: Post a Comment



<< Home

This page is powered by Blogger. Isn't yours?