Thursday, June 11, 2009

 

«ብርቱካንን እወዳታለሁ»

በወርቀ አማኑዕል ዘሰላም
(muziky68@yahoo.com)

ሰኔ 4 ቀን 2001 ዓ.ም

አሜሪካን አገር ተሰድጄ ከወጣሁኝ በርካታ አመት አለፈኝ። አዲስ አበባ የነበርኩኝ ጊዜ የግል ትምህርት ቤት ስለተማርኩኝ እንግሊዘኛ ብዙ አይችግረኝም። ከፈረንጆች ጋር በኢትዮጵያዊ አክሰንቴ ደህና እግባባለሁ። ነገር ግን እንደ አማርኛ የዉስጤን የሃሳቤን መናገር አልችልም።

አንድ ቀን አብሮኝ የሚሰራ የሕንድ ተወላጅ ጓደኛዬ ቤቱ ጋብዞኝ እሄዳለሁ። በዚያ ከሁለት ልጆቹ አንዷ፣ ኮሌጅ ልትገባ አንድ አመት የቀራት፣ በጉጅራቲ(በሕንድ ከሚነገር ቋንቋዎች አንዱ) አባቷን ስታናግር ሰማሁኝ። ልጅቷ በቅርብ ከሕንድ የመታጭ መሰለኝ። ነገር ግን ልጆቹ አሜሪካ አገር እንደተወለዱ ጓደኛዬ ሲነግረኝ ተገረምኩኝ። ለምን ? የማዉቃቸዉ ብዙ ኢትዮጵያዉያን ልጆቻቸዉ አማርኛ የማይናገሩ በመሆናቸዉ !

ይህ ሕንድ እንዴት ልጆቹን በአገሩ ቋንቋ እንዳስተማረ ጠየኩት። «ሙሉ ለሙሉ የወላጆች ጉዳይ ነዉ። ወላጆች ልጆቻቸዉን በሚፈልጉበት መሥምር በልጅነታቸዉ መምራት ካልቻሉ ጥፋቱ ልጆቹ ላይ ሳይሆን ወላጆቹ ላይ ነዉ።” አለኝ። እኔም ያን ጊዜ፣ የኔ ልጆች አማርኛ የሚያወቁ ይሆናሉ ብዬ በዉስጤ ዛትኩኝ።

ጥቂት አመታት አለፉ። ጊዜ መድረሱ አይቀርም፣ እዚሁ አሜሪካን አገር የተዋወኳትን አንዲት የአገሬን ልጅ አግብቼ እናቷን የምትመስል ቆንጅዬ ሴት ልጅ ወለድኩኝ። ከባለቤቴ ጋር ተመካክረን የአማርኛዉን ጉዳይ ከልጃችን ጤንነት ቀጥሎ ትልቅ ቦታ ሰጠነዉ። ይኸዉ አሁን አሥራ ሁለት አመቷ ነዉ፤ ቀልጣፋ የአማርኛ ተናጋሪ ወጥቷታል። ወላጆቻችን ከኢትዮጵያ እኛን ለመጠይቅ ሲመጡ እንደሌሎች የአበሻ ልጆች የኔ ልጅ ተርጓሚ አላስፈለጋትም። ኢትዮጵያ ለጉብኘት ስትሄድም እንደልቧ እያወራች ተቀላቅላና ተሳስቃ ትመለሳለች።

ከአራት ወራት በፊት አንድ ነገር ሆነ። ስልክ ይዤ አወራለሁ። ልጄ ትንሽ ራቅ ብላ ታዳምጣለች። ያናደደኝ፣ ያሳሳዘኝ ነገር እንዳለ አወቀች። ስልኬን ጨርሼ ወደ ሶፋዉ ሄድኩኝና ተቀመጥኩ። እንደመተከዝ ብሎኛል። የምትሰራዉን ትታ ከጎኔ ተቀመጠች። «ምን ሆነሃል ባባ ?» አለችኝ። «ዳዲ» የሚለዉን ስለምጠላዉ «ባባ» ነዉ ልጄ የምትለኝ። (ፈረንጆች ልጆቻቸዉ ዳዲ ይበሏቸዉ ከፈለጉ) «ደህና ነኝ። ምን አልሆንኩኝም » አልኩኝ ያበሳጨኝንና ያሳዘነኝን ለመሸፋፈን ፈልጌ።

ዝም ብላ ለጥቂት ደቂቃ ደረቴ ላይ ከተኛች በኋላ «ብርቱካን ማን ናት ?» አለችኝ። ወዲያው «ክዉ አልኩኝ» ። በስልክ ሳወራ የነበረዉ በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ላይ የደረሰዉን ግፍ በተመለከተና እንዴት አሳዛኝና አሳፋሪ ድርጊት ወያኔ-ኢሓዴግ እንደፈጸመ ነበር። የምመልሰዉ ግራ ገባኝ። ምን እንደምላት አሰላሰልኩና «አንድ ታዋቂ ሴት ናት» የሚል መልስ ሰጠሁ። «ኢትዮጵያ ነዉ የምትኖረዉ? ምን ሆነች ባባ » አለችኝ። «አዎ ኢትዮጵያ ነዉ ያላቸዉ። ታስራለች» አልኩኝ። ጥያቄዉ አላቆመም። «ለምን ታሰረች ? » የሚል ጥያቄ ቀረበ። ቁና ቁና መተንፈስ ጀመርኩኝ። ኢትዮጵያን እንዳትጠላብኝ በኢትዮጵያ የሚደረገዉን ግፍ ልነግራት አልፈለኩ ነበር። እርሷ ግን ለምን እንደሆነ አላወቅም አጥብቃ ጠየቀች።

«ምንም ነገር ሳታጠፋ ነው የታሰረችዉ» አልኳት። «እንዴ ባባ ? ጀጅ የለም እንዴ ? » አለች። «ጀጅ አይደለም ዳኛ ነዉ በአማርኛ የሚባለዉ» ብዬ እርማት ሰጠሁና «ዳኛ አለ። ግን እዚያ ያለዉ መንግስት ጥሩ መንግስት አይደለም። ዝም ብሎ ሰዉ ያስራል። ሰዉ ይገድላል። ሕግ አያከብርም።» አልኳት። ለዚህ ነዉ እናንተ አሜሪካን አገር የመጣችሁት ? አለችኝ። «አዎን ? » ብዬ መለስኩ። «ኢትዮጵያን ጠለኋት ባባ» አለችኝ። ወዲያዉ ዉስጤ ደንግጦ «ይሄማ አይሆንም። ኢትዮጵያ ማለት እኮ እኔ፣ እናትሽ፣ አክስቶሽ፣ አጎቶችሽ ..ማለት ነዉ። ኢትዮጵያን መጥላት ማለት እኛን መጥላት ማለት ነዉ። አንቺን እራስሽንም መጥላት ነዉ።» ብዬ የአሜሪካንን ታሪክ በማንሳት ለማስረዳት ሙከራ ጀመርኩኝ።

አሜሪካን አገር ስለነበረዉ የሲቪል ራይት እንቅስቃሴ በተለይም ስለ ዶር ማርቲን ሉተር ኪንግና ሮዛ ፓርክ ፕሮጀክት ነገር በትምህርት ቤቷ ሰርታ ነበር። ያንን አስታወስኳት። በአሜሪካ የነበረዉን ችግር ፣ እንዴት ጥቁሮች እንደተበደሉ ገለጽኩላት። አሜሪካ መጥፎ ሰዎች ቢኖሩም ጥሩ ሰዎች ብዙ ስለደከሙ አገሪቷን ቀየሯት። ኢትዮጵያንም በተመለከተ ኢትዮጵያን መጥላት ሳይሆን መፍትሄዉ እንደ አሜሪካ ኢትዮጵያን መቀየር ነዉ። እነብርቱካን ልክ ያኔ እነ ማርቲን ሉተር ኪንግና ሮዛ ፓርክ እያደረጉት እንደነበረዉ እያደረጉ ነዉ። ያኔ ማርቲን ሉተር ኪንግ ሳያጠፋ እንደታሰረዉ ነዉ አሁንም ብርቱካን ሳታጠፋ ነዉ የታሰረቸዉ።» አልኳት።

«አንተ ታዉቃታለህ ? » አለችኝ። «አዎ አውቃታለሁ» አልኳት”። «እኔንስ ታወቀኛለች» አለች። «አንቺን አታወቅሽም። ግን ለአንቺና ለሌሎች ልጆች ወደፊት ጥሩ አገር እንዲኖራቹህ ለማድረግ ስትል ነዉ የታሰረቸዉ» አልኳት። «ልጅ አላት» አለችን። «አዎ የአራት አመት ሴት ልጅ አላት።» አልኳት። ያኔ ልጄ ማልቀስ ጀመረች።

ከሁለት ቀናት በኋላ ኮምፒተሬ ላይ ቁጭ ብዬ ስሰራ አሁንም እንደልማዷ እግሮቼ ላይ ቁጭ አለች። «ባባ የብርቱካንን ፎቶ ታሳየኛለህ? » አለችኝ። ወዲያዉ ወደ ድህረ ገጾች ሄጄ አሳየኋት። «ባባ እኔ ብርቱካንን እወዳታለሁ !» አለችኝ። «አንቺ ብቻ አይደለሽም። በኢትዮጵያ ዉስጥ ሕዝብ ሁሉ ነዉ የሚወዳት። አይዞሽ ትፈታለች። እግዚአብሄር ከርሷ ጋር ነዉ። እግዚአብሄር ካለ ደግሞ በአይንሽ ታያታለሽ። ሁልጊዜ ማታ ማታ ግን ከመተኛትሽ በፊት ጸልይላት» አልኳትና ግንባሯን ስሜ አሰናበትኳት።

«አይዞሽ ትፈታለች!» ያልኩት በአይምሮዬ ሕይወት እንዳለዉ እንደሚራመድ ነገር መንቀሳቀስ ጀመረ። ትላንት «ትፈታለች» በማለት አንድ፣ ሁለት እያልን ነበር የምንቆጥረዉ። አሁን አንድ መቶ ስድሳ ስምንት ደርሰናል። «መቼ ነዉ የምትፈታዉ? እንዴት ነዉ የምትፈታዉ ? » የሚሉት ጥያቄዎች በአይምሮዬ ይመላለሱ ጀምር።

በዉስጤ ለጥቂት ደቂቃዎች ብዙ ሃሳቦች ከተጋጩ በኋላ ሁሉም ወደ አንድ መሥመር መጡልኝ። የጠራ ሁኔታ ይታየኝ ጀመር። አሁን ያለዉን አገዛዝ የፖለቲካ ክስረት አየሁ። ብርቱካን ሚደቅሳ እሥር ቤት ሆና የታጠቁ ኃይላት ተጨፍልቀዉ ካደረጉት በላይ በአራት ኪሎ ያሉትን አምባገነኖች እየሸረሸረቻቸዉ እንዳለ ታየኝ።

«ትፈታለች» ከሚለዉ «መቼ መጄምሪያዉኑ ታሰረች» ወደሚለዉ ሃሳብ መጣሁኝ። እርሷ በሥጋ ብትታሰርም በርግጥ የታሰረችዉ እርሷ እንዳልሆነች ገባኝ። ነጻ ሴት፣ የመንፈስ ነጻነት የተላበሰች እንደሆነች አየሁኝ።

የታሰሩትስ፣ አላወቁትም እንጂ፣ ጨካኝ አሳሪዎቿ መሆናቸዉን፣ በሥጋ ያልታሰሩ በመንፈስ ግን ሲታይ በጥላቻ፣ በእብሪት፣ በጭንቀት፣ በክፋት፣ በዘረኝነት የተተበተቡ የአዉሬነት ባህሪ የተላበሱና ወደፊት ለልጅ ልጆቻቸዉና ለዘራቸዉ አንገት መድፊያ ምክንይት የሆኑ እንደሆነ ታየኝ።

የእድሜ ባለጸጋ የሆኑት አምባሳደር እምሩ ዘለቀ «የኢትዮጵያ እምቤት» ሲሉ ለወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ያላቸዉን አክብሮትን ፍቅር ገለጹ። የኔዉ አንድ ፍሬ ልጅ «ብርቱካንን እወዳታለሁ» አለች። ብርቱካን ሚደቅሳ ከልጅ እስከ ሽማግሌ፣ ሴቱን ወንዱም በሙሉ ለአንድ የተቀደሰ ኢትዮጵያ አላማ ወደ አንድነት ያመጣች እንደሆነ እናያለን።






Comments: Post a Comment



<< Home

This page is powered by Blogger. Isn't yours?