Wednesday, June 03, 2009

 

ኢሕአዴግ ከፈለገ ግንቦት ሰባትን ሊያጠፋዉ ይችላል !

ኢሕአዴግ ከፈለገ ግንቦት ሰባትን ሊያጠፋዉ ይችላል !
ግርማ ካሳ
(muziky68@yahoo.com)



እዉቁ አሜሪካዊዉ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪና የሰላም ኖቤል ተሸላሚ የነበሩት ቄስ ዶር ማርቲን ሉተር ኪንግ በተናገሩት አባባል ነዉ ጽሁፌን የምጀመረዉ። «እርስ በርስ መከባበርና መዋደድ ካቃተን ሁላችንም እንጠፋለን» ነበር ያሉት፣ እኝህ በሰላማዊ ትግል ዉስጥ እራሳቸዉን በ39 አመታቸዉ ስዉተዉ፣ አራት ልጆችን አባት አልባ አድርገዉ ያለፉት፣ ታላቅ ሰዉ።

ሰሞኑን የኢትዮጵያ የፖለቲካዉን ደመና ስመለከት ጥሩ ሁኔታ ላይ ያለን አይመስለኝም። ደም ደም እየሸተተኝ ነዉ። የኢሕአዴግ መንግስት በአገሪቷ ያለዉን የፖለቲካ ቀዉስ በሰላም ከመፍታት ይልቅ ተቃዋሚዎችን በሕግ ስም ለመምታት እንዲያስችለዉ «የጸረ-ሽብርተኝነት» ሕግ በሚኒስቴሮች ምክር ቤት አሳልፎ በፓርላማዉ በቅርብ ያጸድቀዋል ተብሎ ይጠበቃል።

በዶር ብርሃኑ ነጋ የሚመራዉ የግንቦት ሰባት ንቅናቄ በበኩሉ በአዲስ አበባ ያለዉን አገዛዝ ሕግ ወጥ የወንበዴ ቡድን ሲለዉ፣ አገዛዙን ለማስወገድ ይረዳዉ ዘንድ፣ አንድ ብሄራዊ የተደራጀ ኢትዮጵያዊ ግንባር (United Ethiopian Command) ለማቋቋም ጥረት ላይ እንዳለ ኢትዮጵያ ሪቪዉ ዘግቧል። እንግዲህ ሁለት ወንድማማቾች ሊተራረዱ ቢላ እየሳሉ እንደሆነ እናያለን።

ሕወሃት ከደርግ ጋር በሚዋጋበት ጊዜ በሃውዜን ትግራይ የተፈጸመዉን ሁላችንም የምናወቀዉ ይመስለኛል። ሕወሃት በዚያ ስብሰባ እያደረገ ሳለ አየር ኃያል ይመጣና ቦምብ ይጥላል። ብዙ የትግራይ ተወላጆች ያልቃሉ። ቦምብ ሲጣልና ንጹሃን ዜጎች ሲያልቁ የሚያሳይ ቪዴዎ ይቀረጻል። ቪዴዎዉን ያየ የትግራይ ተወላጅ ሁሉ ይቆጣል። (እንዴት አየር ኃይል ያን ስብሰባ ሊያዉቅ እንደቻለና በዚያ ቦታ የደረሰዉም እልቂት በተቀናበረ መልኩ በቪዴዮ መቀረጹ የሚያስነሳዉ በርካታ ጥያቄዎች አሉ። ወደፊት በባለሞያዎችና የታሪክ ሰዎች የሚብራራ ይሆናል ብዬ አስባለሁ።)

ይህ የሃዉዜን እልቂት የትግራይ ወጣት ታይቶ በማያታወቅ ሁኔታ ሕወሃትን እንዲቀላቀል አደረገ። የትግራይ ተወላጆች ለመስዋእተነት ቆርጠዉ ሕወሃትን የተቀላቀሉት ዉስጣቸዉ በደርግ ላይ ስላመረረ ነበር። ያመረረ ሰዉ አንዴ ከተነሳ የሚመልሰዉ ነገር የለም።

ታዲያ አሁን የደርግን ቦታ የያዛዉ፣ ከደርግ ይሻላል ብለን የጠበቅነዉ ኢሕአዴግ፣ ዳግማዊ ደርግ ሆኖ፣ እያራመዳቸዉ ባለዉ ጎጂ ፖሊሲዎቹ ብዙዎች እንዲያመሩ እያደረገ እንደሆነ እያየን ነዉ። በተለይም ሰላማዊ በሆነችዋ በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ላይ ኢሕአዴግ በወሰደዉ ኢሰብአዊ፣ ኢፍትሃዊና ጨካኝ እርምጃ በርካታ ኢትዮጵያዊያንን በማይፈልጉበት መንገድ እንዲሄዱ አስግድዷቸዋል። በግንቦት ሰባት አካባቢም የምናየዉም ክስተት ይሄንኑ በግልጽ የሚያሳይ ነዉ።

የግንቦት ሰባት ደጋፊ አይደለሁም። በድርጅቱ ላይ በርካታና የጠነከሩ ትችቶችን አቅርቢያለሁ። የግንቦት ሰባት መፈጠር ጎጂ ነዉ ባይ ነኝ። ነገር ግን አንድ መታወቅ ያለበት ነገር አለ።

የግንቦት ሰባት መሪዎች አብዛኞቹ ጠንካራ የሰላማዊ ትግል ታጋዮች ነበሩ። ለዚህም ማስረጃ እንዲሆን ከምርጫ ዘጠና ሰባት በፊትና የዚያን ሰሞን፣ ዶር ብርሃኑ ነጋ ያስተላልፉት የነበረዉን መልዕክት ማዳመጥና ከቃሊቲ እሥር ቤት ሆነዉ የጻፉትን መጽሐፍ ማንበብ እንችላለን። አንድ ጊዜ እንደዉም በስቶክሆልም ባደረጉት ንግግር፣ ለኢሕአዴግ ከበሬታ ሊኖርን እንደሚገባ ዶር ብርሃኑ ሲናገሩ « ወያኔ ማለት የለብን። አክብረናቸዉ፣ እንዲጠሩ በሚፈልጉት ስም ነዉ መጥራት ያለብን። ኢሕአዴግ ነዉ ማለት ያለብን» ብለዉ ነበር። በመጽሃፋቸዉ ላይ እንደጻፉትም ከአቶ በርከት ስምኦን ጋር ጓደኛሞችና አብረዉ ቢራ ይጥጡ እንደነበረም ገልጸዉልናል። ያን ያህል በኢሕአዴግ ላይ አምኔታ የነበራቸዉ እኝህ ሰዉ በግፍ ከሌሎች የቅንጅት መሪዎች ጋር ቃሊቲ ተወረወሩ። ያኔ ኢሕአዴግ ያደረገዉ ግፍ ዉስጣቸዉን ምሬት እንዲሞላዉ ያደረገ ይመስለኛል።

በተመሳሳይ ሁኔታ የቅንጅት ዋና ጸሃፊ የነበሩት አቶ ሙሉነህ እዮኤልም በሰላማዊ ትግል አቋማቸዉ የጸኑ ሰዉ እንደነበሩ የሚታወቅ ነዉ። እርሳቸዉም በቃሊቲ ተወረወሩ። እንደዉም በተለያዩ የመገናኛ ሜዲያዎች እንዳነበብነዉ ለብዙ ጊዜ እንደርሳቸዉ ያኔ በጨለማ ቤት ዉስጥ እንዲቀመጥ የተደረገ አልነበረም። (አሁን ከአምስት ወር በላይ በጨለማ ቤት ያለችዉ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በብዙ ወራት በለጠቻቸዉ እንጂ)

አቶ አንዳርጋቸዉ ጽጌ በዝዋይ ከብዙ ሺህ ወጣቶች ጋር ታስረዉ በሰደፍ አይናቸዉን የተደበደቡና የኢሕአዴግን የግፍ በትር ለጥቂት ወራትም ቢሆን የቀመሱ ሰዉ ናቸዉ።

እነዚህ አንድ ወቅት የሰላምዊ ትግል አርበኞች የነበሩ ሰዎች፣ አሁን ተስፋ ቆርጠዉ ወደ ማይፈልጉት የትግል መሥመር ተሰማሩ። እርግጠኛ ነኝ፣ የደረሰባቸዉ እስራትና ግፍ ባይደርስባቸዉ ኖሮ ምናልባት አሁን ወደ ደረሱበት ደረጃ ላይደርሱ ይችሉ ነበር። በደርግ ጊዜ ኢሕአዴግን የወለደዉ የሰፊዉ ህዝብ ብሶት እንደነበረ፣ አሁንም ብሶትና ግፍ የግንቦት ስባት ንቅናቄን ፈጠረ ማለት ይቻላል። የግንቦት ስባት አባት ኢሕአዴግ ነዉ።

አሁን ኢሕአዴግ የግንቦት ሰባትን ጉዳይ አጣጥሎ ሊመለከተዉ ይችላል። ከዚህ በፊት ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማሪያም «አሁን ኢትዮጵያን ነጻ የሚያወጣዉ ወያኔ ነዉን ? » ብለዉ እንዳሾፉት ማለት ነዉ። ነገር ግን የኢሕአዴግ ባላሥልጣናት የግንቦት ሰባትን እንቅስቃሴ መናቅ የለባቸዉም እለለሁ።

እንዳሉት ግንቦት ሰባት ወሬ ብቻ ሆኖ ሊቀር ይቻላል። በተለይም ድርጅቱ የሚያወላዉልና የተጨበጠ አቋም ይዞ የማይራመድ ከሆነ፣ በዉጭ አገር ብቻ በሚደረግ እንቅስቃሴ ዉጤት ማምጣት ከፈለገ፣ በፍሎሪዳ እንዳሉ የኩባ ተቃዋሚዎች ጥርስ እንደሌለዉ አንበሳ ማጓራት ብቻ ይሆናል ሥራዉ።

ነገር ግን ሌሎች ድርጅቶችን አስተባብሮ ጠንካራ ግንባር ከመሰረተ ትልቅ ለውጥ ሊያመጣ የሚችልበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል።

በአስመራ ኦነግ፣ ኦብነግ ፣ የአርበኞች ግንባር …የመሳሰሉ ድርጅቶች ለአመታት የትጥቅ ትግል እናደርጋለን ሲሉ ነበር። ኦብነግና ኦነግ አንድ ጎሳ እንወክላለን ስለሚሉ በኢትዮጵያ ህዝብ ድጋፍ ሊያገኙ አልቻሉም። የአርበኞች ግንባር ጠንካራ መሪ አልነበራቸዉ። ስለዚህም የትም ሊደርሱ አልቻሉም።

የግንቦት ሰባት የአመራር አባላት፣ በተለይም በኢትዮጵያ አንድነት ያምናል የተባለዉን በጄነራል ከማል ገልቺ የሚመራዉን ኦነግ ፣ እንዲሁም የአርበኞች ግንባር አቅፈዉ በአረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንድራ ሥር ግንባር ቢመሰርቱ፣ የተመሰረተዉ ግንባር በቀላሉ አለም አቀፍ እዉቅና ሊያገኝ የሚችል ይመስለኛል። በኢትዮጵያዊያንም ዘንድ እነ ዶር ብርሃኑ ነጋና አቶ ሙሉነህ እዮዔል የታወቁ እንደመሆናቸዉ በርካታ ዜጎች፣ የቀድሞ ወታደራዊ መኮንኖች፣ እንዲሁም አሁን በዉትድርና የሚያገለግሉ በቀላሉ ግንባሩን በመቀላቀል ሊያጠናክሩት ይችላሉ።

ይህ ግንብር ሕወሃት ከደርግ ጋር ሲታገል ያደርግ እንደነበረዉ፣ ከአቶ ኢሳያይስ አፈወርቂ ጋር የሚሰራም ከሆነ፣ የጦር መሳሪያ፣ መድሃኒቶች የመሳሰሉትን በቀላሉ ሊያገኝ የሚችልበት ሁኔት ሊፈጠር የሚችል ሲሆን በኤርትራ ወታደሮችን በማሰልጠን ከኤርትራም ሆኖ ከፍተኛ የፖሮፖጋንዳ ዘመቻ በመልቀቀ በአጭር ጊዜ ዉስጥ ጠንካራ ግንባር ሊወጣዉ ይችላል።

በዚህም ሆነ በዚያ፣ አሁን ያለንበት ሁኔታ ካልተሻሻለ፣ ከላይ ለመጠቆም እንደሞከርኩት፣ አገራችን ጦርነት ላይ ተዘፍቃ ከዉርደት ወደ ዉርደት፣ ከድህነት ወደ ድህነት፣ ከሰቆቃ ወደ ሰቆቃ መሄዷ አይቀሬ ነዉ። ምልክቱን እያየን ነዉ። የክተት ዘማቻዎችን እየሰማን ነዉ። እየተሳለ ያለዉ ጎራዴ አንገቱን የሚቆርጠዉን ፈልጎ እያንጸባረቀብን ነዉ።

እንግዲህ ይሄን ሁሉ የምዘረዝረዉ ወደፊት ሊምጣ የሚችለዉን አደጋ በማሳየት አስቀድሞ ለሁላችንም የሚበጀዉንም ሰላማዊ መፍትሄ በጋራ አሁኑኑ ለመፈለግ ወደ ሚያስችለን ደረጀ ሁሉንም ወገኖች በተለይም ኢሕአዴግን ለመግፋት ነዉ። ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማሪያም ወያኔ-ኢህአዴግን ያናንቁ እንደነበረዉ አቶ መለስ ዜናዊም ተመሳሳይ አስተሳሰብ ኖሯቸዉ በጡንቻና በጉልበት፣ ጠመንጃ ያነሱትን እጨፈልቃለሁ ብለዉ የሚያስቡ ከሆነ የደረቁ ዛፎች በሞሉበት ጫካ እሳት እንደለኮሱ ተደርጎ የሚወሰድ ነዉ።

የግንቦት ሰባት ንቅናቄን የወለደዉ ኢሕአዴግ እራሱ ነዉ። የግንቦት ሰባትን ንቅናቄ እያጠናከረ ያለዉ ኢሕአዴግ እርሱ ነዉ። ኢሕአዴግ የግፍ አገዛዙን በጨመረ ቁጥር፣ በኢሕአዴግ ላይ ያለዉ ጥላቻና ምሬት እያደገ ይመጣል። ጥላቻዉና ምሬቱ ደግሞ ሰዉን ወደ ማይፈልገዉ ደረጃ ይወስደዋል። ነፍጥ እንዲያነሳ ያደርገዋል።

እስከአሁን የተደራጀ ኢትዮጵያዊ ኃያል ስላልነበረ ነፍጥ ለማንሳት የሚፈልግ ከነበረ ምንም ማድረግ አልቻለም ይሆናል። ከአሁን በኋላ ግን፣ ከሃዉዜን እልቂት በኋላ የትግራይ ወጣቶች ወደ ሕወሃት ካምፖች እንዳመሩት፣ አሁን ደግሞ የከፋዉና የመረረዉ ወደ ግንቦት ሰባት ፊቱን ያቀናል። (እንደሚወራዉም ከሆነ በርካታ ኢትዮጵያዊያን በተለይም ከጎጃምና ከጎንደር ድንበር እያቋረጡ ኤርትራ እየሄዱም ነዉ)

ይሄንን ነዉ ኢሕአዴግ የሚፈልገዉ ? ጦርነት ነዉ ኢሕአዴግ የሚፈልገዉ ? እነ አቶ መለስ ደርግን ከመጣላቸዉ በፊት ከወጣትነት እድሜ ጀምሮ ጦርነት ላይ ነበሩ። ስባት አመት በስላም ከገዙ በኋላ እንደገና ከኤርትራ ጋር ጦርነት ጀመሩ። እስከአሁን ድረስ በመሰረቱ ከኤርትራ ጋር «ጦርነት» ላይ ናቸዉ ማለት ይቻላል። በሶማልያ ጋር ለሁለት አመት ጦርነት ዉስጥ ነበሩ። እስከ መቼ ይሆን እነዚህ ሰዎች ጦርነትን የሚናፍቁት ? መቼ ይሆን በሰላም መኖር የሚመርጡት ?

እኔን ምክረን ቢሉኝ «ኳሱ በሜዳቹህ ነዉ። ብትፈልጉ በአገራች ያለዉ ችግር በሰላም እንዲፈታ፣ ጦርነት አስከፊ ነዉና አገራችን ወደ ጦርነት እንዳትዘፈቅ ሰላምዊ መፍትሄ እንዲመጣ ማድረግ ትችላላቹህ» ነበር የምናላቸዉ።

«እንዴት ነዉ ወደ ጦርነት ወደ እልህ ወደ መጠፋፋት እየወሰደን ያለዉን ዝንባሌ፣ አቅጣጭዉን መቀየር የምንችለዉ ?» የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። አንዳንድ ሃሳቦችን እንደሚከተለዉ ልዘርዝር ፡

መጀምሪያ እኛም ወንዶች ሆነን መተኮስ እንደምንችል ሌሎችም መተኮስ እንደሚችሉ ማወቅ ያስፈልጋል። ማንም ከማን አያንስም።

ሁለተኛ እንደ ኢትዮጵያዉያን ሌሎችን በሕግ ስም «ለምን ነፍጥ አነሱ ? ሽብርተኞች ናቸዉ» ብሎ ከመክሰስ ይልቅ፣ ነፍጥ ያነሱበትን ምክንያት መርምረን ነፍጥ ላነሱበት ጉዳዮች በሰላም በትህታ ዘላቂነት ያለዉን መፍትሄ መፈለግ አለብን።

ሶስተኛ ኢሕአዴግ በርግጥ ግንቦት ሰባትና ሌሎች በርሱ ላይ የተነሱ ድርጅቶች እንዲጠፉ ከፈለገ ቀላል መንገዶች አሉት። ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን ያለ አንዳች ቅደመ ሁኔታ በአስቸኳይ ቢፈታ፣ በኢትዮጵያ የጠበበዉን የሰላምዊ ፖለቲካ መድረክን ቢያስፈ፣ በሚቀጥለዉ አመት የሚያደረገዉ ምርጫ ነጻና ፍትሃዊ እንዲሆን ሁኔታዎች ቢያመቻች፣ ለአገሪቷም ለሕዝቡም ለራሱም ለኢሕአዴግ የሚበጅ ነዉ ብዬ አምናለሁ። ኢትዮጵያዉያን በሰላማዊ ትግል ላይ ያላቸዉ እምነት ይጨምራል። እንደ ግንቦት ሰባት አይነት ድርጅቶችን ከመደገፍ ይቆጠባሉ። (ምናልባትም የግንቦት ስባት መሪዎችም እርሳቸዉ «ነገሮች ተስተካክለዋል» ብለዉ ድርጅታቸዉን በራሳቸዉ ፈቃድም ሊያከስሙትና የሰላምዊዉን ትግል እንደገና ሊቀላቀሉ ይችሉም ይሆናል)

ኢሕአዴግ በጭፍን፣ እልህ የተሞላበት፣ ግትርና ኋላቀር ፖለቲካ ተያዘ እንጂ፣ ግንቦት ሰባትን ለመምታት ከሚያወጣዉ የጸረ-ሽብርተኝነት ረቂቅ ሕግ ይልቅ የአንዲቷ የብርቱካን ሚደቅሳ መፈታት መቶ እጥፍ የግንቦት ስባትን ግለት ( Momentum) ሊቀንሰዉ ይችላል።

በርግጥ ግንቦት ሰባት ንቅናቄን እንደወለደዉ ሁሉ ሊያጠፋዉ ይችላል። በጉልበት ግን አይደለም - በሰላም።









Comments: Post a Comment



<< Home

This page is powered by Blogger. Isn't yours?